በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።
ኢትዮ ቴሌኮም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ኩባንያው ባለፈው የ2018 በጀት ዓመት ያስመዘገበውን ስኬት መነሻ በማድረግ፣ በ2019 ዓ.ም የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግ፣ ገቢውን ለማሳደግ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት በርካታ ግቦችን ማቀዱን አስታውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በመግለጫው እንደተናገሩት በ2019 በጀት ዓመት የቴሌኮም መሰረተ ልማትን ይበልጥ ለማዘመን የ5G እና 4G የኔትወርክ ተደራሽነትን ለማሳደግ ታቅዷል።
ተቋሙ ባለፈው አንድ ዓመት የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት አበረታች ውጤቶች ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በ2019 በጀት ዓመት የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ይበልጥ የሚያንቀሳቅሱ አዳዲስ አሰራሮችና አገልግሎቶች እንደሚተገበሩ ተናግረው፤ 295 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።
በ2019 ዕቅድ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ 1ሺህ 628 ተጨማሪ አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች የሚገነቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 605 ያህሉ በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎችና የቴሌኮም አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑን አብራርተዋል።
የ4G አገልግሎት ለተጨማሪ 300 ከተሞች ተደራሽ የሚደረግ ሲሆን፣ ይህም የአገልግሎቱን ተደራሽነት 95 በመቶ ያደርሰዋል ብለዋል።
የ5G አገልግሎት ለተጨማሪ 40 ከተሞች እንደሚዳረስና በአጠቃላይ የ5G ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር ወደ 83 ከፍ ይላል ብለዋል።
ተቋሙ ባደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል የገመድ አልባ ሞባይል ኔትወርክ አቅም በመፍጠር፣ አጠቃላይ የማስተናገድ አቅሙን ወደ 135 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያሳድጋል ብለዋል።
በፊክስድ ብሮድባንድ አገልግሎት ላይ የሚታዩ የአገልግሎት መቋረጦችን ለማስወገድና የአገልግሎት ጥራትን ከፍ ለማድረግ ተጨማሪ 150 ሺህ ደንበኞችን የተሻለ የፋይበር ቴክኖሎጂ የማዛወር ስራ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
በከተሞች የሚገኘውን የፋይበር መስመር በመጨመር 300 ኪሎ ሜትር በማስፋፋት አጠቃላይ አቅሙን ከ15 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ከፍ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ያስቀመጣቸውን እነዚህን ግቦች ለማሳካት የቴክኖሎጂ አጋርነቱን እንደሚያጠናክር እና በሰው ሃይል ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።