ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል

ጋምቤላ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የምግብ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ ከተቀመጠው  ስትራቴጂካዊ የግብርና ምርቶች መካከል ሩዝ አንዱና ዋነኛው ነው:: 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሩዝ ልማት በሀገሪቱ የግብርና ፖሊሲ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት እየተከወነ ይገኛል::

በተለይ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት በተያዘው አገራዊ አቅጣጫ መሠረት ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።


 

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድሩው ቱት ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ክልሉ ለሩዝ ልማት አመቺ  በመሆኑ አርሶ አደሩ በዘርፉ ለመሰማራት የሚያሳየው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።

በተለይም በአኝዋህ እና በማጃንግ ዞኖች በሩዝ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች አበረታች ውጤት እያገኙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የተገኘውን አዎንታዊ ውጤት በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በማስፋት፣ አገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሩዝ መፈልፈያ ማሽኖችን እና ምርታማ የሆኑ አዳዲስ የሩዝ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

እንደ ሩዝ ልማት ያሉ የተመረጡ የግብርና ኢኒሺቲቮች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር፣ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጋቸውንም አክለው ገልፀዋል።

የአቦቦ ወረዳ አርሶ አደር እስማኤል ሁሴን፤ በአካባቢያቸው ሩዝ በማልማት በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።

በመሆኑም በሩዝ ልማት ዙሪያ የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል አካባቢው ያለውን እምቅ ተፈጥሮአዊ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ በዲማ ወረዳ የኮይ ቀበሌ የልማት ጣቢያ ባለሙያ አቶ ተረፈ ታፈሰ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም