በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማፋጠን ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ እና ለተቀመጡ ግቦች መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው-ዋምኬሌ ሜኔ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማፋጠን ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ እና ለተቀመጡ ግቦች መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው-ዋምኬሌ ሜኔ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማፋጠን ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና ለተቀመጡት ግቦች መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ፀሀፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የአፍሪካን አህጉራዊ ውህደት ማጠናከር፣ የምርት አቅምን ማሳደግ፣ንግድን ማብዛትና ማስፋፋት፣ እንዲሁም የተቋማትን አቅም ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
ስብሰባው አፍሪካ ወደ ጥልቅ ውህደት በፍጥነት እየተጓዘች ባለችበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአህጉሪቱ ውስጥ ትኩረቱ ከድርድር ወደ አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በተግባር ወደ መፈጸምና ውጤት ወደ ማምጣት እየተሸጋገረ መሆኑንና አስፈላጊ የነበሩት ሁሉም ፕሮቶኮሎች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህን ፕሮቶኮሎች በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአህጉር አቀፍ ንግድ ጠንካራ የሕግ መሠረት መጣሉንና ተለዋዋጭ አህጉራዊ ገበያ ለመፍጠር ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማሳደግ የአህጉራዊ ጥረቱ አስፈላጊ አካል መሆኑን ጠቅሰው የአፍሪካ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ተስፋ እውን የሚሆነው ችግሮችን በቆራጥነት በመጋፈጥና እርምጃዎችን በመውሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢኮኖሚዎችን ለማዋቀር፣ ኢንዱስትሪያዊ ልማትን ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የአፍሪካን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን ለማሳካት እድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን በተግባር የሚያስፈጽሙ አገራት 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ያለበትን እና በአጠቃላይ 3.4 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያለውን ሰፊ ገበያ የማግኘት ዕድል እንደሚኖራቸው አመላክተዋል።
በ2024 እ.ኤ.አ. የአፍሪካ አህጉር ውስጥ ንግድ 220 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ የተመዘገበ ሲሆን፣ የዚህ ንግድ ትልቁ ድርሻም በኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው አፍሪካ እሴት በተጨመረባቸው ምርቶች ላይ የበለጠ እየነገደችና ባልተዘጋጁ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የምታደርገው ንግድ እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማፋጠን ለቀጠናው ሀገራት ብቻ ጠቃሚ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ትግበራ እና ለተቀመጡት ግቦች መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የተሻለ ትስስር ያለው ቀጣና፣ የበለጠ ቀልጣፋ ድንበሮች፣ ጠንካራ የምርት አቅም እና እየሰፋ የሚሄድ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር የአፍሪካን አንድ የጋራ ገበያ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።