ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ስኬት ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ስኬት እና ለሁሉም ተሳታፊ ሀገራት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ገንቢ ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኗን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒቬቲቭ የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስብሰባው የቀጣናዊ ውህደትን ወሳኝ ጠቀሜታ ያሳያል ብለዋል።

የቀጣናው ሀገራት በጂኦግራፊ፣ በታሪክ፣ በባህል እንዲሁም እየጨመረ በመጣው የጋራ የኢኮኖሚ ፍላጎት የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የበለጠ ጥልቅ የቀጣናዊ ውህደት ሂደት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የሥራ ዕድል ፈጠራን የማፋጠን መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ የጋራ የመቋቋም አቅም እና የመረጋጋት መሠረት መሆኑን አንስተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ራዕይን ወደ ተጨባጭ እውነታ ለመቀየር ቁልፍ መንገድ ነው ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ ኢንቨስትመንቶችን ለማስተባበር፣ ፖሊሲዎችን ለማጣጣም እና ንግድንና ትስስርን የሚያደናቅፉ ማነቆዎችን ለመፍታት የተቀናጀ ማዕቀፍ እንደሚሆን አመላክተዋል።

በዚህ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት መንገዶች፣ ድንበሮችና የንግድ ኮሪደሮችን ከማሻሻል ባለፈ፣ መተማመንን የሚገነባ፣ ተቋማትን የሚያጠናክርና ለሕዝቦቻችን ዕድሎችን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ስኬት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ለዚህም ቀጣናዊ ውህደትን በልማት ስትራቴጂ ማዕከል በማድረግ ለቀጣናዊ ኮሪደሮችና ንግድን ማመቻቸት የሚያገለግሉ መሠረተ ልማቶች ከጎረቤት ሀገራትና ከአጋሮቻችን ጋር በቅርበት በመሥራት ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ፖለቲካዊና ቴክኒካዊ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢኒሼቲቩ ለሁሉም ተሳታፊ ሀገራት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ውይይትን በማስፋፋት፣ ፖሊሲዎችን በማጣጣምና ልምዶችን በመለዋወጥ ገንቢ ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከቀጣናዊ ውህደት ዓላማዎች ጋር በቅርበት የተሳሰረ መሆኑን አመላክተዋል።


 

ኢትዮጵያ የንግድ ስርዓቷን እና የጉምሩክ አሠራሯን ለማዘመን፣ የንግድ ሥራ አካባቢን ለማሻሻልና ቁልፍ ተቋማትን ለማጠናከር ትልልቅ እርምጃዎችን መውሰዷን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም ግልጽነትንና በሕግና በደንብ የተመራ የንግድ ሥርዓትን ያጠናክራል ብለዋል።

እንዲሁም ቀጣናውን የሚያስተሳስሩ ስትራቴጂካዊ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ኮሪደሮች ላይ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከቀጣናዊ ቃል ኪዳኖች ጋር የሚጣጣሙና እርስ በርስ የሚያጠናክሩ ማሻሻያዎችን ለማስፈጸም ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያሉ ብለዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች ግልጽ፣ ወደፊትን ያማከለና በዜጎች ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ወደ ተጨባጭ እውነታ የሚቀይሩ ተግባራዊ እርምጃዎች ላይ እንዲተኮርም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም