የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው
ቦንጋ፤ ነሐሴ28/2018(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ እድገትና ደህንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።
የጥንታዊ ስልጣኔ መነሻና በአንድ ወቅት ስሟም ከሀያላን ሀገራት ተርታ የነበረችው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ የነበራት ተሰሚነትና የወደብ ባለቤትነት ለገናናነቷ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ይሁን እንጂ በታሪክ አጋጣሚ የቀይ ባህር ባለቤት ከነበረችበት ከተነጠለች ጀምሮ የራሷ የባህር በር በማጣቷ ለበርካታ ችግሮች ተዳርጋ ቆይታለች።
በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ያለቸው ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ቢኖራትም ወደብ አልባ መሆኗ በእድገቷና በኢኮኖሚዋ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮባታል።
ይህን ታሪክ በመቀየር ኢትዮጵያን በቀጣናው ሀገራት ወደነበረችበት ከፍታ ለመመለስ የባህር በር ባለቤትነትን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ዘሪሁን ያሬድ፣ የባህር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የደህንነት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የባህር በር ባለቤትነት ኢትዮጵያ በቀጣናውና በአሁጉሩ ያላትን ስትራቴጂካዊ ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳድግ ነው።
የአካባቢውን ሀገራት የህዝብ ለሕዝብ ትስስር በማጠናከር ቀጣናዊ ውሕደትን ለመፍጠር፣ ሰላምን ለማጽናትና የጋራ እድገትን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የባህር በር መኖር ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ በማስቀረት ለሀገር ልማት እንድታውል ያደርጋል ያሉት መምህሩ፣ የወጪና ገቢ ምርቶችን በቀላሉ በማሳለጥ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነቷንም እንደሚያሳድግ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆን በዲፕሎማሲዊ መንገድ የጀመረችው ጥያቄ መልካዓ ምድራዊና ሕጋዊ መሠረት ያለው በመሆኑ የዜጎችን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም መምህሩ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን ማሞ በበኩላቸው፣ ቀይ ባህር ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በዲፕሎማሲዊ መስክ ትልቅ ቁርኝት የነበረውና የሕልውናዋ መሠረት መሆኑንም ገልፀዋል።
በወቅቱ ኢትዮጵያን በዓለም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ዘርፎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ከነበሩ አራት ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡
የባህር በር ማጣት በተዘጋ ቤት ውስጥ እንደመኖር መሆኑን የጠቀሱት መምህሩ፣ መልሶ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የሚደረገው ጥረት የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን በጋራ ተደጋግፎ ለማደግ ካለው ፋይዳ ባለፈ ለቀጣናው ሰላም መከበር ትልቅ ዋጋ እንዳለውና የኢትዮጵያም ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳድግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡