የኢትዮጵያን በውሃ ሃብቷ የመልማት መብት ግብጽ ልታከብር ይገባል - ቲቦር ናዥ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን በውሃ ሃብቷ የመልማት መብት ግብጽ ልታከብር ይገባል - ቲቦር ናዥ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን በውሃ ሃብቷ የመልማት መብት ግብጽ ልታከብር ይገባል ሲሉ የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ገለጹ።
ከቀይ ባህር ጋር ታሪካዊ ቁርኝት ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ ተገቢና ህጋዊ መሰረት ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።
ቲቦር ናዥ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ግብጽ በአባይ ተፋሰስ ላይ ምንም አይነት የውሃ ድርሻ ሳይኖራት ለዘመናት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ስትጠቀም መቆየቷን አውስተዋል።
ግብጽ የዓባይ ወንዝ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ሊኖረኝ ይገባል በሚል የምትከተለው አካሄድ ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ ካለው የቀጣናው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታ ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም መሆኑንም ገልጸዋል።
ግብፅ አዲሱን እውነታ መቀበል አለባት ያሉት የቀድሞው ዲፕሎማት፤ የኢትዮጵያን ፈጣን ዕድገትና በቀጣናው እየተቀየረ ያለውን የኃይል ሚዛንም አንስተዋል።
የቀጣናው ፖለቲካዊ ገጽታ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን የገለጹት ቲቦር ናዥ፣ ግብፅ በአሁኑ ሰዓት አዲስ የኃይል ሚዛን መፈጠሩንና ኢትዮጵያም እጅጉን ማደጓን ልትገነዘብ እንደሚገባ አስምረውበታል።
ግብፅ የድርድር አቀራረቧን ዳግም በመመርመርና አዲስ እና አዎንታዊ አመለካከት ይዛ ወደ ንግግር ጠረጴዛው ከተመለሰች ዘላቂና ፍትሃዊ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም ነው ያነሱት።
የሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብቶችን የመጠቀም መብት እውቅና መስጠት ላይ የተመሰረቱ ውይይቶች የጋራ መግባባት ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ቲቦር ናዥ የኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሃብት መጠቀም ራስ ወዳድነት ወይም በግብፅ ላይ የህልውና አደጋ ተደርጎ መታየት የለበትም ሲሉ አስገንዝበዋል።
አገራት የራሳቸውን የተፈጥሮ ሃብት ይጠቀማሉ። ሁሉንም ነገር በእውነታው ላይ ቆመን እንመልከት ብለዋል።
ቲቦር ናዥ አያይዘውም፤ ግብፅ ስለ ዓባይ ከምታነሳው አቋም በተቃራኒው፣ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር እንዳትደርስ የያዘቸውን አቋም ምክንያታዊነት የጎደለው መሆኑን አንስተዋል።
ግብፅ የቀይ ባህር ዳርቻ ሀገራት ብቻ የባህር አስተዳደር ጉዳይ ይመለከታቸዋል የምትል ከሆነ፣ በአባይ ተፋሰስ መጠቀም ያለባቸው የውሃ ድርሻ ያላቸው ሀገራት ብቻ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ከእውነታ ጋር የማይጣጣመውን ይህን የግብጽን አቋም የግብዝነት ድርጊት ሲሉ ተችተውታል።
የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዠ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተም ሀሳባቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበራትን የባህር ላይ ታሪክ በማስታወስ፣ ሀገሪቱ በወቅቱ የራሷ የባህር ኃይል (ኔቪ)፣ የባህር ኃይል ማዕከል እና በባህር ኃይል ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ የኢትዮጵያ አድሚራሎች እንደነበሯትም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት እጅግ አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ አሁን የምታደርገውን የባህር በር የማግኘት ጥረት ለቀይ ባህር ካላት ታሪካዊ ግንኙነት ጋር አያይዘውታል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ፍትሃዊና ሕጋዊ ጥያቄ መሆኑን የገለጹት ቲቦር ናዥ፣ የጎረቤት ሀገራት የኢትዮጵያን ፍላጎቶች በሚገባ መረዳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።