የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉና የተቀላጠፈ አገልግሎት መሰጠቱ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ እመርታ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉና የተቀላጠፈ አገልግሎት መሰጠቱ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ እመርታ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል
ወላይታ ሶዶ፤ ነሐሴ 28/2018(ኢዜአ)፦ የመንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የተቀላጠፉ አገልግሎቶች መሰጠት መጀመሩ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ እመርታ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት የተሻለ እድገትና ማንሰራራት እንዲመጣ ማድረጉ ይታወቃል።
በተለይም የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን በማሻሻል፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ተኪ ምርቶች እንዲበራከቱ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ግልጽና ገበያ መር የሆነ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ ስርዓት በመዘርጋቱ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተሳትፎ በእጅጉ እያደገ መምጣት ችሏል።
በመሆኑም በመንግስት የተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የተቀላጠፉ አገልግሎቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉ ትልቅ እመርታ እንዲመዘገብ ያስቻሉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ዲን ኢንጂነር መንግስቱ መና፤ የመንግስት የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የተቀላጠፉ አገልግሎቶች ለኢንዱስትሪ ዘርፉ እመርታ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማምረት አቅም በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን በተጨማሪ ተኪ ምርቶችን በማምረት ለኢኮኖሚው መነቃቃትና ለበርካታ ዜጎችም የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪያል አስተዳደርና ኢንጂነሪንግ ኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ጌታሁን ሶርሳ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ስኬት አበረታች ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በብዛትና በጥራት በማምረት የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ መቀነስ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ዘርፉ የውጭ ምንዛሪን ማዳንና ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እያገዘ በመሆኑ እነዚህን መልካም ጅምሮች ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።