በአማራ ክልል ዲጂታል 2030ን በተሳካ መልኩ እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ዲጂታል 2030ን በተሳካ መልኩ እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዲጂታል 2030ን በተሳካ መልኩ እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለፀ።
በባሕር ዳር ከተማ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።
በአውደ ርዕዩ የመክፈቻ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው እንደገለጹት፤ የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማ በክልሉ ዲጂታል 2030 ን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማሳየትና ማስተዋወቅ ነው።
አውደ ርዕዩ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የፈጠራ ሥራዎቻቸውንና የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ለሕዝብና ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አብራርተዋል።
ይህም የቴክኖሎጂ ፈጠራን በማስፋፋት የተያዘውን ሀገራዊና ክልላዊ የዲጂታላይዜሽን ግብ ለማሳካት እየተሠራ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በኤግዚቢሽኑ በተለያዩ ተቋማት የለሙ 35 የተለያዩ ዲጂታል ሥርዓቶች (Digital Systems) በይፋ ተመርቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።