ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ከመኸር ሰብል የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከ2018/19 የመኸር ሰብል የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት የሚያስችሉ የሰብል እንክብካቤ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በተያዘው የምርት ወቅት የታቀደውን የምርት መጠን ለማሳካት የእርሻ መሬትን በአግባቡ አዘጋጅቶና ግብአቶችን ተጠቅሞ በዘር ከመሸፈን በመቀጠል ሰብሉን ከአረም፣ ከነፍሳትና ከተለያዩ በሽታዎች መከላከል ወሳኝ ነው።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ከዚህ አኳያ አርሶ አደሩን ዘመናዊና ባህላዊ የሰብል ጥበቃ ዘዴዎችን አቀናጅቶ እንዲጠቀም ባለሙያዎችን መድቦ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከመኸር አዝመራ የተሻለ ምርት በመሰብሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።


 

በክልሉ በምርት ዘመኑ ከ11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ380 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥም እስካሁን 9 ሚሊዮን 627 ሺህ 749 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸዋል።

ምርታማነትን ለመጨመር የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ መቻሉን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በዚህም 5 ሚሊዮን 158 ሺህ 516 ሄክታር የሚሆነው መሬት በትራክተር መታረሱን አስረድተዋል።

ከግብዓት አቅርቦት አንጻርም ከቀረበው ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ7 ሚሊዮን 677 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

አቶ ጌቱ እንደተናገሩት የታቀደውን ምርት ለማሳካት በተለይም የተቀናጀ የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።

አርሶ አደሩ ማሳቸውን በየጊዜው በመከታተልና በመፈተሽ የበሽታና የአረም ቁጥጥር ሥራዎችን በልዩ ትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እንዲሁም አርሶ አደሩ በደቦ ባህላዊ የመረዳዳት ስልት በመጠቀም የኩትኳቶና አረም የመንቀል ተግባርን በሰፊው እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሰብል እንክብካቤና ጥበቃ ስራውን ለማጠናከርም የአረም እና ተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም በተቀናጀና በተናበበ አሰራር በተከናወኑ ስራዎች በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቁመና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም