የመደመር እሳቤ ለኢኮኖሚ ትንሣኤ፡የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ፍሬዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ ለኢኮኖሚ ትንሣኤ፡የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ፍሬዎች
ሀገራችን በማካሄድ ላይ ያለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሁሉን አቀፍ፣ ዘርፈ ብዙና አካታች ነው፡፡በአግባቡ ከተተገበረ መሠረታዊና ዘላቂ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ያስገኛል።ይህም እውን የሚሆነው በአንዴ ሳይሆን በሂደት ነው፡፡የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚታየውን ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መዛባት ለማስተካከል፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ የኢኮኖሚውን ቀጣይ ዕድገት ለማረጋገጥ፣ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በተሻለ መልኩ እንድትጠቀም ለማድረግ፣ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያለንን ግንኙነትና ተወዳዳሪነት ለማጎልበት፣ የሥራ ዕድልን ለማስፋት፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ በጥቅሉ ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ የሚሆንበትን የብልጽግና ትሩፋት ለማሳደግ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተነሣ በሚቀጥሉት ዓመታት የኢኮኖሚው ዕድገት ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ምርትና ምርታማነት ያድጋል፤ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሐዝ ይወርዳል፤ የመንግሥትን ገቢ የማሳደግና ለልማት የሚውል ሀብት በዋናነት ከሀገር ውስጥ ምንጮች የማሰባሰብ አቅም ይጎለብታል፤ የወጪ ንግድ ይስፋፋል፤ የውጭ ሐዋላ ፍሰት ያድጋል፤ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይጨምራል፤ የሥራ ዕድል ይስፋፋል፤ ከኢኮኖሚው ዕድገት፣ ከብሔራዊ ባንክ የቁጥጥርና የሱፐርቪዥን አቅም መጎልበት እንዲሁም ከቴክኖሎጂ መስፋፋትና ከውጭ ባንኮች የመግባት ዕድል ጋር ተያይዞ የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማነት፣ ዕድገትና ተወዳዳሪነት ይጠናከራል፡፡ በጥቅሉ፣ ሀገሪቱ በአካባቢዋም ሆነ ከሰሐራ በታች ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች መካከል በቀዳሚነት እንደምትቆም ይጠበቃል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ከላይ የተገለጸ ቢሆንም፣ አንዳንድ አሉታዊ ጫናዎችን እንደሚያስከትል ታሳቢ ተደርጓል።በመሆኑም፣ መንግሥት በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማርገብ የሚረዱ በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ያለውን ድጎማ በጊዜያዊነት ለመቀጠል፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ደሞዝ ለማሻሻልና በከተማም ሆነ በገጠር የሴፍቲኔት መርሐ ግብርን አጠናክሮ ለማስኬድ በገባው ቃል መሠረት በየደረጃው ተፈጻሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ከዚህ ሌላ፣ ጊዜያዊ ወጪዎችንና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ የሚረዳ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች እንደሚገኝ ቃል ተገብቷል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ አጋሮች በሚቀጥሉት ዓመታት ለኢትዮጵያ ለመስጠት ያቀዱት ትልቁ የተቀናጀ የገንዘብ ርዳታ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የዋጋና የውጭ ኢኮኖሚ የማረጋጋት፣ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነትና ዕድገት የማረጋገጥ ቁልፍ ሚናዎቹን ለመወጣት የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በተለይም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን የሚያረግብባቸውን አዳዲስ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል ጀምሯል። የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ ጠንካራ የገቢ መሠረት ለመጣልና የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ (ለምሳሌ፣ ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር መውሰድን የመሳሰሉ) የመበደሪያ ስልቶችን ሳይጠቀም የመንግሥት ወጪን ለማሳደግ የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየተገበረ ይገኛል፡፡