የተኪ ምርት ስትራቴጂካዊ ሚና - ኢዜአ አማርኛ
የተኪ ምርት ስትራቴጂካዊ ሚና
የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን መዛባት በዘላቂነት ለመቅረፍ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እያካሄደ ይገኛል።
ይህ የተኪ ምርት ስራ ጅማሮ በዋናነት ያነጣጠረው በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬን በሀገር ውስጥ በማስቀረት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ላይ ነው።
ቀደም ሲል የነበሩ የተበታተኑ የማምረት ሙከራዎችን ወደ ተቋማዊ አሰራር ለመቀየር ይፋዊ የተኪ ምርት ስትራቴጂ በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ስራ ገብቷል።
ይህ ስትራቴጂ ለቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚቆይ ፍኖተ ካርታ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ለትግበራው መፋጠን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ እንደ ትልቅ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ሀገራዊ ንቅናቄው በ2016 ዓ.ም ተግባራዊ መሆን ለጀመረው ብሔራዊ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው።
የስትራቴጂው መውጣት እና ወደ ተግባር መግባት በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማስገኘት ጀምሯል።
ትልቁ እና ዋነኛው ፋይዳም የውጭ ምንዛሬን ማዳን ሲሆን በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ በተመረቱ ተኪ ምርቶች ከ5 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ አምራቾች በገበያ ላይ ያላቸው የምርት ድርሻ ወደ 45 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የፋብሪካዎች አማካይ የማምረት አቅምም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ብሏል።
ይህ መነቃቃት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ ከመሆኑም በላይ የፋብሪካዎችን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ከሀገር ውስጥ የግብርና እና የማዕድን ምርቶች ጋር በማስተሳሰር የአቅርቦት ሰንሰለቱን አጠናክሮታል።
ይህንኑ ሀገራዊ ጥረት እና የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ መድረኮች ላይ የዘርፉን ስልታዊ ጠቀሜታ በተደጋጋሚ አንስተዋል።
በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የምግብ እና የማዳበሪያ አቅርቦት መስተጓጎል በመጥቀስ፣ የሀገር ውስጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ኢትዮጵያን የምግብ እጥረት እንደታደጋት ገልጸዋል።
ተኪ ምርት ለኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነት እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ይወጣባቸው የነበሩ የድንጋይ ከሰል እና የችፑድ ምርቶች አሁን ላይ በሀገር ውስጥ በስፋት እየተመረቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
የሀገር ውስጥ አምራቾች ጥራትን መሰረት አድርገው በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከተኪ ምርት ስራዎች ያገኘውን ስኬት ይበልጥ ለማስፋት እና ዘላቂ ለማድረግ አዳዲስ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን እና ግቦችን አስቀምጧል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተያዘው አዲስ በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ አምራቾችን የገበያ ድርሻ ወደ 49 ለማድረስ እና የውጭ ምንዛሬ ቁጠባውን ወደ 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ለዚህም ስኬት አምራቾች ጥሬ ዕቃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ እና ምርቶቻቸውን ያለ ደላላ ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችል የዲጂታል የገበያ ትስስር ፕላትፎርም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ይፋ ተደርጓል።
ወደፊትም ከቀላል የሸማች ዕቃዎች ባለፈ እንደ ተሽከርካሪዎች፣ ኬሚካሎች እና ብረታብረት ያሉ አስራ አምስት ስልታዊ የከባድ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ትኩረት የሚደረግ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመተካት ባለፈ የማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ላይ ተወዳዳሪ የማድረግ ሰፊ ራዕይ ተሰንቋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የተኪ ምርት ስራ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ከውጭ ጥገኝነት ወደ ሀገር ውስጥ ምርታማነት እያሸጋገረ የሚገኝ ስልታዊ እርምጃም ነው።
በጥናት የተለዩት 96 ቁልፍ ስልታዊ ምርቶች በሙሉ አቅም ወደ ማምረት መሸጋገራቸው ለሀገር በቀል እውቀትና ለፈጠራ ስራዎች ሰፊ በር ከመክፈቱም በላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ላይ ያላትን የድርድር እና የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም በእጅጉ ያጠናክረዋል።