ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የተጀመረው የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባሀርዳር፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርአት በመዘርጋት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የተጀመረው የተቀናጀ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(/) ገለፁ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የጤና ስርአት ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል።

ሙሉነሽ ደሴ(/) በወቅቱ እንደገለፁት መንግስት የጤና ዘርፉን ለማሻሻል መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በዚህም ጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርአት በመዘርጋት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው እስካሁን በተከናወኑ ጤና ተቋማትን የመገንባት፣ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን የማሟላትና አገልግሎትን የማሻሻል ስራዎች ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።


 

በህገ-ወጥ መንገድ በሚገቡ መድሃኒቶች፣ ምግቦችና ደረጃቸውን ባልጠበቁ የህክምና መሳሪያዎች ላይ የሚደረግ የቁጥጥር ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

ይህም ጥራት ያለው፣ ፈጣንና ፍትሃዊ የህክምና አገልግሎት በመስጠት በህብረተሰቡ ዘንድ የበለጠ መተማመንን ለመገንባት ያስችላል ሲሉ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃለፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የሚካሄዱ ተግባራትን በቅንጅት ለመምራት በተከናወነ ስራ አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።


 

በተለይም ህገ ወጥ መድሃኒቶችን፣ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦችን እንዲሁም ከደረጃ በታች የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን ለመቆጣጠር የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የከተማ አሰተዳደር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም