የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመደመር መንግስት የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲመራ ይፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዓመታት በፊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የህዝብ ቅሬታ ከሚስተዋልባቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ ነበር። አሁን ግን ታሪክ ተቀይሯል ነው ያሉት።
በዓመት የማይስተናገድ ዜጋ ጉዳዩን በቀን ውስጥ ፈፅሞ የሚመለስበት ተቋም ሆኗል። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ግብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቋማዊ ሪፎርምና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎች የተቋሙን ስምና የሥራ ባህል በአዲስ መልክ እየቀየሩ ነው ብለዋል።
በተለይም አገልግሎቶቹን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ማሸጋገሩ ተገልጋዮች ፈጣን፣ ግልጽና እንግልትን የቀነሰ አገልግሎት እንዲያገኙና እርካታቸውም እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
አገልግሎቱ በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ራሱን በማደራጀት የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት፣ የቪዛ፣ የጉዞ ሰነዶች፣ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲሁም የአየርና የመሬት ድንበር ቁጥጥርን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን በውጤታማነት እያከናወነ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
እያንዳንዱ ሪፎርም የሚለካው ዜጎች በሚያገኙት የአገልግሎት ጥራት፣ በሚቆጥቡት ጊዜና በሚያገኙት እርካታ ነው።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋማዊ ለውጥም መንግሥት ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂና ዜጋ-ተኮር የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በቀጣይም የተቋሙን የዲጂታል ሽግግር በማፋጠን፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ጥራትን በማሳደግ፣ ተቋማዊ ዐቅሙን በማጠናከር እና የተገልጋዮችን እርካታ በተጨባጭ በማረጋገጥ ላይ መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የተገልጋዮችን ሐሳብና ቅሬታ ራስን ለማሻሻል መነሻ አድርጎ መቁጠር ከተቻለ ከዚህም በላይ መለወጥ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።