ቀጥታ፡

‎የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ልምድ ለማካፈል ወጣቶች ወደተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሊያቀኑ ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ልምድ ለማካፈል ወጣቶች ወደተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሊያቀኑ መሆኑ የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አባንግ ኩመዳን ገለጹ።

ከመላው የሀገሪቱ የተውጣጣ የወጣቶች ቡድን በሦስት የአፍሪካ ሀገራት ነገ የሚጓዝ ይሆናል።

የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባንግ ኩመዳን እንደገለጹት፤ ወጣቶቹ የሚጓዙት ጋና፣ ዚምባብዌና ናይጄሪያ ነው።

በዚህ የጉዞ መረሃ ግብር ሀያ አራት ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በመትከል ልምድ እንደሚያካፍሉም አስታውቀዋል።

መርሃ ግብሩ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም የብልጽግና ወጣት ክንፍ በፓኪስታን የችግኝ ተከላ ማካሔዳቸውን ገልጸዋል።

የልዑካኑ ጉዞ የልምድ ልውውጥ ከማድረግ በተጨማሪ ወንድማማችነትን ለማጠናከር የሚያግዙ ተግባራትን እንደሚያከናውን  አስታውቀዋል።

በቀጣይም ወጣቶች ወደ ተለያዩ ሀገራት በመሄድ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በማከናወን የኢትዮጵያን ልምድ የማካፈል ተግባርን ያጠናክራል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በስኬታማነት እየተከናወነ ይገኛል።

በዚህ ዓመት ብቻ ከ800 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአንድ ጀምበር መተከላቸው ይታወሳል።

ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዓለም አቀፍ እውቅና እያገኘ ሲሆን የተለያዩ ሀገራትም ተሞክሮውን እየወሰዱት ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም