ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማስፋት የሚያስችላትን ቋሚ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ከፈተች - ኢዜአ አማርኛ
ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማስፋት የሚያስችላትን ቋሚ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ከፈተች
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2018(ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከል ያለውን የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የብራዚል ንግድ እና ኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ኤጀንሲ (አፔክስብራዚል) ቋሚ ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ከፍቷል።
በመክፈቻው መርሃ ግብር ከፍተኛ የኢትዮጵያ እና የብራዚል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ቋሚ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ መክፈቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተጨባጭ ስትራቴጂካዊ ቅንጅት መጀመሩን የሚያበስር መሆኑን ገልፀዋል።
አፔክስብራዚል ለኢንቨስተሮች የመረጃ እጥረቶችን በማስወገድ፣ አካባቢያዊ የገበያ መረጃ በመስጠት እና የንግድ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የብራዚልን የላቀ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ልምድ ከኢትዮጵያ ሰፊና ለም መሬት ጋር በማጣመር በቡና፣ በምርጥ ዘር ፣ በእንስሳት ሀብት እና ዘመናዊ አግሮ-ቢዝነስ ላይ መስራት ያስችለዋል ሲሉ ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለሚገቡ የብራዚል ኩባንያዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ክዣንዲር ፈሬራ ዶስ ሳንቶስ እንደተናገሩት፤ አፔክስብራዚል በአዲስ አበባ ቋሚ ጽሕፈት ቤት መክፈቱ በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ማደጉን የሚያሳይ እና ወደፊት ለመድረስ ያለውን ታላቅ ምኞት የሚያንጸባርቅም ነው ብለዋል።
ጽሕፈት ቤቱ የብራዚል ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ገበያ አማራጮችን እንዲገነዘቡ፣ አጋሮችን እንዲያገኙ እና የገበያ መረጃዎችን እንዲያገኙ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባለሀብቶችም በዓለም ትልልቅ ኢኮኖሚዎች በአንዱ በሆነችው ብራዚል ውስጥ ያሉ እድሎችን እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል ብለዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መዲና በመሆኗ አፔክስብራዚል ከኢትዮጵያ ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ እና በሰፊው የአፍሪካ ገበያ እንደ ግብርና፣ አቪዬሽን፣ መድኃኒት ማምረት፣ መሠረተ ልማት እና ታዳሽ ኃይል ባሉ ዘርፎች ያሉ እድሎችን እንድትጠቀም ያደርጋታል ሲሉ ገልፀዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) በበኩላቸው አፔክስብራዚል በአዲስ አበባ ቋሚ ጽሕፈት ቤት መክፈቱ በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከል ባለው የኢኮኖሚ አጋርነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።
የአፔክስ ጽሕፈት ቤት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስርን የበለጠ ለማሳደግ፣ የንግድ አጋርነትን ለማመቻቸት እና በኢትዮጵያ እና በብራዚል ባለሀብቶች መካከል ትርጉም ያለው እና ተጨባጭ ትስስርን ለማስፋፋት የሚያገለግል መድረክ እንደሚሆንም ተናግረዋል።