ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ደቡብ ምዕራብና መካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ) ፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ምዕራብ፣ሰሜን ምዕራብ፣ደቡብ ምዕራብ እና መካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከነሃሴ 26 ቀን ጀምሮ እስከ ጳጉሜን አምስት ቀን 2018ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ የሚኖረውን የአየር ፀባይ ሁኔታ በተመለከተ ለኢዜአ መግለጫ ልኳል።

በመግለጫውም ነሀሴ ወር የክረምት የመጨረሻ ወቅት በመሆኑ በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናብ መጠን እንደሚቀንስ በማመላከት ለረጅም ጊዜ ደረቅ ሆነው የሰነበቱት ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸውን እንደሚያስተናግዱ ጠቁሟል።

በምሥራቅ፣ በሰሜን ምሥራቅና በመካከለኛው ኢትዮጵያ አካባቢዎች የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚቀነስ ነገር ግን በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስርጭትም በመጠንም የተሻለ ዝናብ እንደሚያገኙ በመግለጫው ተመላክቷል።

በሚቀጥሉት አስር ቀናትም ምዕራብ፣ሰሜን ምዕራብ፣ደቡብ ምዕራብ እና መካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።

ማኅበረሰቡም ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የሚኖረውን የእርጥበት ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የግብርና ስራቹን እንዲያከናውን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ከሚያስተናግዱ ቦታዎች መካከል ቄለም ወለጋ፣ ኢሉባቦር የምዕራብ ፣መካከለኛ ፣ደቡብ እና ሰሜን ጎንደር፣ የሰሜን፣ የምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች፣ ካማሺ፣ መተከል፣ አሶሳ ዞኖች እንደሚገኙበት ከመግለጫው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሁሉም ሸዋ ዞኖች፣ አኝዋክ፣ ከፋ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ጉራጌ ፣አዲስ አበባ ፣ድሬዳዋ፣ የምዕራብ ፣የሰሜን ምዕራብ ፣መካከለኛው፣ ምሥራቅ እና ደቡብ ትግራይ ዞኖች ፣የሲዳማ አብዛኛው የክልሉ ዞኖች ደግሞ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ከሚያስተናግዱ አካባቢዎች መካከል መሆናቸው ተጠቁሟል።

ኢንስቲትዩቱ ቀላል፣መካከለኛ እና ከባድ እርጥበትን የሚያስተናግዱ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ፣ የመኸር ሰብል አብቃይ ፣ አርብቶ አድርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይህን የአየር ሁኔታ ለግብርና ስራዎቻቸው እንዲያውሉ አስገንዝቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መካከለኛ እና ከባድ የዝናብ መጠን የሚያስተናግዱ አካባቢዎች ተደፋታማ ማሳዎች ላይ የተዘጉ የማፋሰሻና የማንጣፈፊያ ቦዮች ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሰብል በሽታን አረምን አስቀድሞ መከላከል ፣የአፈር መሸርሸር ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን፣ እና አርሶ አደሮችም የማሳ ጉብኝት በየጊዜው በማድረግ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስቧል።

ከቀላል እስከ መካከለኛ እርጥበት የሚያገኙ ቦታዎች ደግሞ የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል፣ የዝናብ ውሀን በማሰባሰብ በደረቅ ወቅቶች መጠቀም ፣የአፈር ውስጥ ትነትን መጠንን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ፣የእንስሳት ግጦሽ ሳርን በአግባቡ መያዝ ተገቢ ነውም ተብሏል።

ለተከታታይ አስር ቀናት የሚቆየው አየር ፀባይ ሁኔታም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም