ከምስራቅ ቦረና ዞን ቆላማ ወረዳዎች ከዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
ከምስራቅ ቦረና ዞን ቆላማ ወረዳዎች ከዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል
ነገሌ ቦረና፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ከዘንድሮው የበልግ አዝመራ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በምስራቅ ቦረና ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝርእት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ከ176 ሺህ 20 ሄክታር በላይ መሬት በበልግ አዝመራው በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን አስታውሰዋል፡፡
በልማቱ ከተሳተፉት 143 ሺህ 288 ከፊል አርብቶ አደሮች መካከል 23 ሺህ 614 ሴቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች ከለማው ከዚሁ መሬት 2 ሚሊዮን 126 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ አጠቃላይ ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡
በዞኑ የበልግ አዝመራ ከተመረቱት የሰብል አይነቶች መካከል ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ቦለቄ፣ ማሽላና ሰሊጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ዘንድሮ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከበልግ አዝመራ የተሰበሰበው አጠቃላይ ምርት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ያለው ነው ብለዋል፡፡
በበልግ አዝመራው ልማት ከተሳተፉት የዞኑ ነዋሪዎች መካከል የነገሌ ቦረና ከተማ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አቶ አበራ ሞገስ ከበልግ አዝመራ ካለፉት አመታት ሁሉ የተሻለ ምርት መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡
የተሻሻለ የግብርና አሰራር፣ የምርት ማሳደጊያ አጠቃቀምና የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት መኖሩ ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
የኩታ ገጠም አስተራረስ፣ በመስመር መዝራትና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ከተሻሸሉ የግብርና አሰራሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በምስራቅ ቦረና ዞን ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ ወር የዝናብና የዘር፣ ከሐምሌ እስከ ነሔሴ ወር ደግሞ የምርት መሰብሰቢያ ወቅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡