በቅርሶች ምዝገባ፣ እድሳትና ልማት ላይ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያንሰራራ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቅርሶች ምዝገባ፣ እድሳትና ልማት ላይ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያንሰራራ አድርገዋል
ባህር ዳር ነሐሴ 27/2018(ኢዜአ)፡-በቅርሶች ምዝገባ፣ እድሳትና ልማት ላይ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያንሰራራ እያደረጉ መሆኑን የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረኩን በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ እንደገለጹት፤ በመንግስት ኢኒሼቲቭ የተገነቡትን የጎርጎራና ሎጎ ሃይቅ ሪዞርቶች ከነባር የመስህብ ሀብቶች ጋር በማስተሳሰር ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ያሉ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን ለመሳብ የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ማስገኘቱንም ገልጸዋል።
በተለይም ቱሪዝሙ በሚቀዛቀዝበት የክረምት ወቅት እንደ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄና እንግጫ ነቀላ ያሉ ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ የጎብኝዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በስፋት ወደ ክልሉ እንዲመጡ በማድረግ፣ የክልሉን ኢኮኖሚ ከማነቃቃት ባለፈ ህብረተሰቡን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳስቻለም ነው የጠቀሱት።
በመጪው አዲስ ዓመት፣ በመስቀልና በሌሎች በዓላትም ወደ ክልሉ የሚመጡ ጎብኝዎችን ቁጥርን በተሻለ መልኩ ለማሳደግ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የቢሮው የዕቅድ፣ በጀት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብርሃኔ በበኩላቸው ፤በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 121 ቅርሶችን በመጠገን፣ 5 ሺህ 766 ተንቀሳቃሽና 190 ቋሚ ቅርሶችን በመመዝገብ ለቱሪዝም ልማት ማዋል ተችሏል ብለዋል።
በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም በበጀት ዓመቱ ከ18 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ፤ ከ58 ሺህ 300 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የክልሉን የመስህብ ሀብቶች በመጎብኝታቸው ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።