የህዳሴ ግድብ ግንባታን ያሳካ ታሪካዊ ትውልድ የባህር በር ጥያቄንም ያሳካል - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታን ያሳካ ታሪካዊ ትውልድ የባህር በር ጥያቄንም ያሳካል
ደሴ ፣ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ) ፦ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በማሳካት ታሪክ የሰራው ይህ ትውልድ የባህር በር ባለቤትነትንም እውን በማድረግ ለሌላ ታሪክ መትጋት አለበት ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለረጅም ዘመናት የቀይ ባህር ዳርቻዎችና ወደቦች ባለቤት ሆና የቆየች ቢሆንም፣ በየጊዜው በነበሩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ጂኦፖለቲካዊ ሁነቶች ምክንያት የባህር በር አልባ እንድትሆን መደረጓ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የሀገሪቱ የህዝብ ብዛት፣ እያደገ የመጣው ኢኮኖሚ እና የመልክዐ ምድራዊ አካባቢዋ ተፈጥሯዊ ቁርኝት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የባህር በር መብቷን እንደገና እንድታስከብር የሚያስገድድ መሆኑም ይታወቃል።
የአርበኞች ማህበር አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የቀድሞ የሰራዊት አባላት፣ ለሀገር ተቆርቋሪ ምሁራንና ሌሎችም ይህ ታሪካዊና ህጋዊ እውነት በትውልዶች መካከል ሳይደበዝዝ እንዲቀጥል የነበራቸውን ድርሻ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ወሎ ዞን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ጽህፈት ቤት አባላት፤ በቀይ ባህር ቅርብ እርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ የሚያስቆጭ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ መደረጉ በሴራ የተፈፀመ የባንዳነት ተግባር መሆኑን ያነሱት አርበኞቹ አሁን ላይ ይህንን የቆየ ስብራት ለመጠገን በመደመር መንግስትና በህዝቡ የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ፀሐፊ ተተኪ አርበኛ አየለ ወልደ ጊዮርጊስ፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅ የተደረገበት ምክንያት እስካሁን ለማንም ግልጽ ያልሆነና የምንቆጭበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የህዳሴ ግድብ ግንባታን በማሳካት ታሪክ የሰራው ይህ ትውልድ የባህር በር ባለቤትነትንም እውን በማድረግ ለሌላ ታሪክ መትጋት እንዳለበት አንስተዋል።
በዚህ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸው ለስኬቱም የሁላችንም ሀገራዊ አደራ እና ሃላፊነት አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ተዘግቶባት መዝለቅ የማትችልና የህልውናዋ ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄው መልስ ሊያገኝ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የማህበሩ አባል አቶ ማሞ አያሌው እና ሃምሳ አለቃ አለማየሁ አበበ፤ ለኢትዮጵያ የባህር በር ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን የትውልዱ መረዳት አስደናቂነት አንስተው ለተግባራዊነቱ በጋራ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የቀይ ባህር መልክዓ ምድራዊ ቁርኝት ከጥንት ጀምሮ ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን አንስተው በዚህ ዘመን የባህር በር የምትነፈግበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይችልም ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ቀይ ባህርን ለመነጠል የተሄደበት ርቀት የሴራ ፖለቲካ ውጤት መሆኑን ያነሱት ሌላኛው የማህበሩ አባል ሃምሳ አለቃ ባለሟል መለሰ፤ ኢትዮጵያ ታሪኳን አድሳ የባህር በር ባለቤት የምትሆንበት ጊዜ ብዙም እሩቅ ሊሆን አይችልም ብለዋል።
በወቅቱ የነበሩ ፖለቲከኞች የሰሩት ታሪካዊ ስህተት ኢትዮጵያን አሁን ላይ ብዙ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን የሚናገሩት ሃምሳ አለቃ ባለሟል መለሰ፤ የባህር በር ባለቤትነቷ እውን እንዲሆን በመስራት ታራካችንን የምናድስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክዐ ምድርና በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ተገቢ ጥያቄ መሆኑም ተናግረዋል።