በጅግጅጋ ከተማ የመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማ እንዲሆን የቅድመ ዝግጀት ሥራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ የመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማ እንዲሆን የቅድመ ዝግጀት ሥራ ተከናውኗል
ጅግጅጋ፣ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማ እንዲሆን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ።
በከተማው የ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ነው።
በጅግጅጋ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ትምህርት ቤቶች ለ2019 የትምህርት ዘመን ለመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማነት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የጅግጅጋ ካህ አንድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ከድር ረሺድ እንደገለጹት፣ በመጪው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩ ስራ ውጤታማ እንዲሆንና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከወዲሁ እየተሰራ ነው ።
በትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ዝግጁ የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚገቡ ከ1 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የጅግጅጋ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ሰኢድ ንጋቱ በበኩላቸው በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት የመማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ የቤተ-ሙከራ፣ የቤተ መጻህፍትና የአይሲቲ አገልግሎቶችን የማደራጀትና ዝግጁ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ።
ትምህርት ቤቱ በትምህርት ዘመኑ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር በቂ ዝግጅ አድርጓል ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ገልጸው በአዲሱ የትምህርት ዘመንም ከመደበኛ የትምህርት አገልግሎት ባለፈ የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኑር መሀሙድ እንደገለጹት በጅግጅጋ ከተማ ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ የሚያስተምሩ 238 የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ ።
በሁሉም ትምህርት ቤቶች በ2019 የትምህርት ዘመን ከ120 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።
በትምህርት ዘመኑ ለመማር ማስተማሩ ስራ ስኬታማነት የመማሪያ ክፍሎችን የማስተካከልና የቤተ ሙከራና የቤተ መጻህፍት አገልግሎቶችን የማደራጀት ዝግጅቶች በቅንጅት መከናወናቸውን አስታውቀዋል ።