የመስኖና የሜካናይዜሽን ሽግግር በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ከተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኞቹ ናቸው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖና የሜካናይዜሽን ሽግግር በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ከተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኞቹ ናቸው-ምሁራን
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ምሁራን አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና መደገፊያ የሆነው የግብርናው ዘርፍ፣ ለዘመናት በባህላዊ ማረሻና በዝናብ ውኃ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።
ይህ ሁኔታ አገሪቱን ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖና ለምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተተገበሩ ያሉ የስንዴ መስኖ ልማት፣ የበጋ መስኖ አመራረት እና የግብርና መሣሪያዎች ሜካናይዜሽን የዘርፉን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እየቀየሩት ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ግብርናውን ከባህላዊ አሰራር በማላቀቅ ወደ መስኖ ልማት፣ ሜካናይዜሽንና ዘመናዊ አመራረት ለማሸጋገር ሰፊ የፖሊሲና የትግበራ ስትራቴጂዎችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የእንስሳት ሥነ-ምግብ መምህርና ተመራማሪ ዋሲሁን ሀሰን (ዶ/ር) በግብርናው ዘርፍ የታዩ ለውጦች ከምርት መጠን በላይ የአመራረት ሥርዓቱን የሚቀይሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይም የመስኖ ልማት መስፋፋቱ ግብርናው ከዝናብ ጥገኝነት እንዲላቀቅ ያስቻለ ሲሆን፣ ይህም የምርት ወቅትን በማስፋት በዓመት በተለያዩ ወቅቶች ምርት ለማምረት ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ሌላው የግብርናው ዘርፍ ለውጥ ማሳያ የሆነው ሜካናይዜሽን መስፋፋቱ መሆኑን ምሁሩ አመልክተዋል።
በዚህም ከባህላዊ የማረሻ ዘዴዎች በመሻገር ትራክተሮችንና ሌሎች የግብርና ማሽነሪዎችን በመጠቀም የማረስ፣ የማጨድና የመውቃት ሥራዎችን በሜካናይዜሽን ለማከናወን የተደረገው ጥረት በግብርናው ላይ እየታየ ላለው ፈጣን ለውጥ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በሰው ጉልበት የሚወስደውን ጊዜ እና የምርት ብክነትን በመቀነስ ምርትን በጥራትና በብዛት ለማሳደግ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
በተጨማሪም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መስፋፋቱ ኢትዮጵያ ከራሷ የስንዴ ፍላጎት አልፋ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ያስቻላት ዋና የግብርና ለውጥ መሆኑን አስረድተዋል።
የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴም በጓሮ እርሻ፣ በዶሮ እርባታና በንብ ማነብ የተሠሩ ሥራዎች የቤተሰብ የምግብ ስርዓትን ከማሳደግ ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ለማመንጨት ዕድል መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የግብርና እና ዕንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን እና የአፈር ልማት፣ የሰብል እንክብካቤና ንጥረ-ነገር ባለሙያ ሰለሞን ቱሉ (ዶ/ር) ናቸው።
በዚህም የወተትና የእንቁላል ምርት መጨመሩን ጠቁመው፣ በገጠርና በከተማ የሚገኘው ማኅበረሰብ በእነዚህ የግብርና ሥራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ከእህል ምርት ባሻገር በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተሠሩ ሥራዎችም ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እንደ አብነት አስረድተዋል።
በተለይም የአቮካዶ ምርት መስፋፋትና የቡና ምርት ኤክስፖርት ከፍተኛ ገቢ ማስገኘታቸው በዘርፉ ከታዩ ዋና ዋና ለውጦች መካከል መሆኑን ጠቁመዋል።
ከምርቱ ማደግና መስፋፋት በተጨማሪ ግብርናው ባለፉት አመታት ለበርካቶች የስራ ዕድል የተፈጠረበት ነው ብለዋል።
በየአካባቢው በኩታ ገጠም ተደራጅተው የሚያመርቱ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች ከራሳቸው አልፈው ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠሩበት መሆኑን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ ለውጦች የኢትዮጵያን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነትና ከባህላዊ አሰራር በማሻገር ወደ መስኖ፣ ሜካናይዜሽንና ዘመናዊ አመራረት እያሸጋገሩት ያሉ ዋና ማሳያዎች መሆናቸውን ምሁራኑ ገልጸዋል።
ይህም የምግብ አቅርቦትን ከማሻሻል ባለፈ የገቢ ምንጭን፣ የሥራ ዕድልንና የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ እያበረከተ ያለውን ሚና ያሳያል ብለዋል።