በክልሉ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ተኪ ምርቶችን የማምረት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ተኪ ምርቶችን የማምረት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን
አሶሳ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ተኪ ምርቶችን የማምረት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአሶሳ ከተማ በግል ባለሃብት የተገነባውን የአሶሳ ዱቄት ፋብሪካ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ፋብሪካው በ120 ሚሊየን ብር የተገነባ ሲሆን ለ40 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩ ተመላክቷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን በወቅቱ እንደገለፁት፤ ክልሉ ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋትና እሴት የተጨመረባቸውን የፋብሪካ ውጤቶች እንዲያመርቱ እየተደረገ ነው ።
የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትም ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እየተቻለ መሆኑን ጠቁመው ይህም የውጪ ምንዛሬን ወጪን ለማስቀረት እና በቂ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ክልሉ ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላውን ድጋፍ በማድረግ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
የአሶሳ ዱቄት ፋብሪካ በከተማው ለሚገኙ የዳቦ ፋብሪካዎች ምርቱን በማቅረብ ከሌላ ቦታ የሚመጣን የዱቄት ወጪ ለመቀንስና ፍላጎትና አቅርቦትን ለማስተካከል አቅም የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል ።
የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 71 አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው ወደሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
አሶሳ ዱቄት ፋብሪካ በክልሉ በቅርቡ ወደሥራ ከገቡ ዘጠኝ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ መሆኑን አቶ አመንቴ አንስተዋል።
የአሶሳ ዱቄት ፋብሪካ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ዮሐንስ ወንዳፈራው፤ ፋብሪካው በቀን 420 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸው፤ ከስንዴ ዱቄት ባሻገር በቀጣይ የቦቆሎ ዱቄትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ለማቅረብ ማቀዱን አብራርተዋል።
ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆን ምርት ለማምረት የሚያስችል የእርሻ ማሳ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
በተያያዘም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መርቀው የከፈቱ ሲሆን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የጨርቃጨርቅ ምርቶችና ውጤት ቀርበዋል።