የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል- ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ./ር) - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል- ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ./ር)
ባህርዳር፤ ነሃሴ 27/2018 (ኢዜአ)፡- የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ./ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አማራጮችን በማስፋትና በማሳለጥ ረገድ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥርና ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓትን መከተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምርት እንቅስቃሴ በአግባቡ እንዲሳለጥና ኢኮኖሚው ላይ እመርታዊ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ሥራዎችን ማከናወን ተገቢ መሆኑን አንስተው፣ ለዚህም ቅንጅታዊ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግሥት ለሦስቱም ዘርፎች በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ በዘርፉ እመርታዊ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
በተለይ የመንገድ መሠረተ ልማትን በመገንባት ተደራሽነቱን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት የተመዘገበባቸው በመሆኑ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ክፍተቶችን ለይቶ በማረም የመንገድ መሠረተ ልማት ትስስሩን ለማሳለጥ በትኩረት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ስምሪትና ሌሎች ተግባራት የሚስተዋለውን ውስንነት በመቅረፍ ሕዝቡ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ተሠርቷል ብለዋል።
በተጨማሪም የሎጂስቲክስ አቅምን በማሳደግ በክልሉ የሚመረተውን ምርት ከብክነት በጸዳና በጥራት አከማችቶና አጓጉዞ ለገበያ ለማቅረብ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ዘርፎቹ በአዲሱ በጀት ዓመትም በውጤታማነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ተቀናጅቶና ተባብሮ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈጻጸም የተሻለ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚህ ስኬት በመነሳትም በተያዘው በጀት ዓመት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የተሻለ እመርታ ለማስመዝገብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።
የዚህ መድረክም ዋና ዓላማ የዘርፉን ስኬቶች ለማስቀጠል፣ ድክመቶችንና ጎደሎዎችን ለማስተካከል በሚያስችል መልኩ ለመገምገም መሆኑን ገልጸዋል።
ለሌሎች ሴክተሮችም የዕድገት መሠረት የሆነውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በትብብርና ቅንጅት መምራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት አገልግሎት ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩ ለቀጣይ ሥራ መሠረት ነው ብለዋል።