የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሕግ ታራሚን ከማረም ማነጽ ባሻገር በተለያዩ የሙያ መስኮች ስብዕናን በመገንባት አምራች የሚሆኑበትን ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሕግ ታራሚን ከማረም ማነጽ ባሻገር በተለያዩ የሙያ መስኮች ስብዕናን በመገንባት አምራች የሚሆኑበትን ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሕግ ታራሚን ከማረም ማነጽ ባሻገር ስብዕናን በመገንባት በተለያዩ የሙያ መስኮች አምራች የሚሆኑበትን ዕድል መፍጠሩን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ገለጹ።
ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚካሄዱ የሪፎርም እርምጃዎች አሰራርን በማዘመን፣ የታራሚዎችን መብትና ደኅንነት መጠበቅ ያስቻለ ውጤት እየተገኘ ነው።
ተቋማዊ የሪፎርም እርምጃዎችም የሰው ኃብትን በማብቃትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጎልበት የአሰራር ሥርዓትን የሚያዘምን ምኅዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥም በሁሉም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሕግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶችና ክብር በመጠበቅ የሚቆዩበት ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ለሕግ ታራሚዎች የሚሰጡት የትምህርትና ሥልጠና፣ የሥነ-ልቦና ግንባታ ተግባራትም ታራሚዎች ወደ አምራችነት የሚሸጋገሩበትን ሙያዊ ክህሎት እያዳበረ ነው ብለዋል።
በዚህም ታራሚዎች ሙያዊ ክህሎትን በማበልጸግ ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ እና ከማረሚያ ቤት ሲወጡም ቀጣይ ሕይወታቸውን የሚመሩበትን ዕድል ፈጥሯል።
በቀጣይም ለታራሚዎች የሚደረጉ የሙያዊ ክህሎት ማጎልበቻ ትምህርትና ሥልጠናዎችን በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ደስታ አስመላሽ በበኩላቸው፤ ለሕግ ታራሚዎች የሚሰጡ የሥነ-ልቦና፣ የመደበኛ ትምህርትና ሥልጠናዎች የተለያዩ ሙያዊ ክህሎቶችን የሚሰንቁበትን ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።
ይህም በተለያዩ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ደረጃዎች ድረስ እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት የሚያመጡ የሕግ ታራሚዎችም የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን በርቀት የሚከታተሉበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በሌላ መልኩም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሠረት የኮሚሽኑን የአገልግሎት፣ የግዥና ፋይናንስ አሰራሮች በኦንላይን የሚሰጡበት ዘመናዊ ምኅዳር መፈጠሩን አንስተዋል።
በቀጣይም የሕግ ታራሚዎችን ከማረም ማነጽ ባሻገር ተቋማዊ የሪፎርም ተግባራትን በማላቅ ለዲጂታላይዜሽን አሰራር ሥርዓት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራበት አስረድተዋል።