ቀጥታ፡

በአፍሪካ አደጋዎችን ለመቋቋም በቴክኖሎጂ የተደገፈና በትብብር ላይ የተመሰረተ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ የአየር ንብረት መዛባትንና መሰል አደጋዎችን ለመቋቋም በቴክኖሎጂ የተደገፈና በትብብር ላይ የተመሰረተ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን የብሔራዊ የልማት ዕቅዷ አካል ማድረጓም ተገልጿል።

የአፍሪካ ቀጣና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም ፎረም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ይፋ የተደረገ ሲሆን እስከ 2027 እያንዳንዱን ሰው በአየር ንብረት ለውጥ መዛባትና በተፈጥሮ አደጋዎች መጠበቅ የሚያስችል ኢንሼቲቭ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከተመድ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቢሮና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የአፍሪካ የተቀናጀ አይነተ ብዙ አደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ እርምጃ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሀና አበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፎረም ወቅታዊና ተገቢ ነው። 

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ድርቅ፣ ጎርፍ እና ሌሎችን አደጋዎችን በተደጋጋሚ እያስተናገደች መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሴቶችና ህፃናት ጨምሮ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች የአደጋው ገፈት ቀማሽ እየሆኑ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የውስጥ የፋይናንስ አቅምን ማጎልበትና ተቋማዊ አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአፍሪካ የአየር ንብረት መዛባትና መሰል አደጋዎችን ለመቋቋም በቴክኖሎጂ የተደገፈና በትብብር ላይ የተመሰረት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን የብሔራዊ የልማት ዕቅዷ አካል ማድረጓን ጠቅሰው፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በፋይናንስና ሌሎችም ተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ማንም ሀገር ብቻውን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስትራቴጂን ውጤታማ ማድረግ እንደማይችል ገልጸው፤  ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራትና የተለያዩ አጋር አካላት ጋር በአይነተ ብዙ የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።


 

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የዘላቂ አካባቢና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሀርሰን ኒያምቤ፤ በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን በማጠናከር ማህበረሰቡን አደጋን የመቋቋም አቅም መገንባትና ከአደጋ መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2027 እያንዳንዱን ሰው ከአየር ንብረት ለውጥ መዛባትና መሰል አደጋዎች መጠበቅ የሚለውን ግብ ለማሳካት ውይይቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጎርፍና የተራዘመ ደርቅ፣ በማህበረ-ኢኮኖሚ፣ እና በሌሎች አደጋዎች ተጋላጭነት ተባብሶ መቀጠሉን በመግለጽ፤  አፍሪካውያን ውስጣዊ ትብብራቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

አደጋ ድንበር የለውም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን በአይነቱ ብዙ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት የአባል ሀገራቱን አቅም ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ቢሮ ዳይሬክተር ኤግነስ ኪጃዚ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት የአመራር ቁርጠኝነት እያደገ በመምጣቱ መሻሻል እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች በፍጥነትና በተወሳሰበ ሁኔታ ተባብሰው ቀጥለዋል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመቆጣጠር የቅደመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና በሀገራት የተቀናጀ አሰራር መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የ2027 ግብ ጠቃሚ መሰረት መሆኑን በመግለፅ፤ በአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ለቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ግንባታ ዘላቂና እምነት የሚጣልባቸው መሆን አለባቸው ብለዋል።

በአፍሪካውያን መካከል ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ ተቋማትን መገንባት እንደሚገባ በመጥቀስ፤ የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም