ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን በሰብል ዝርያዎች ምርምርና በመነሻ ዘር ብዜት በትኩረት እየተሰራ ነው

መተማ፣ ነሐሴ27/2018 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በሰብል ዝርያዎች ምርምርና በመነሻ ዘር ብዜት ተግባራት ላይ በማተኮር እየተሰራ እንደሚገኝ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ። 

ማዕከሉ እያካሔደ ባለው የዘር ብዜትና ማላመድ ስራ ላይ ያተኮረ የጉብኝት መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

በማዕከሉ የቅባትና ጭረት ሰብሎች ምርምር ባለሙያ አቶ እንዳልካቸው አክሊሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ማዕከሉ የደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ አካባቢዎች የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለማውጣት፣ ለማላመድ ፣ ለሰብል አያያዝና ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ምርታማነትን በማሳደግ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በዚህም በያዝነው ክረምት በምዕራብ ጎንደር ቆላማ አካባቢዎች በ100 ሄክታር መሬት ላይ 17 የሰብል አይነቶች የዘር ብዜት እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 


 

ከሁለት ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለዘር አባዥ አርሶ አደሮችና ተቋማት በመስጠት የዘር ብዜትና የማላመድ ተግባሩን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም በቅርቡ ምርታማነታቸው ተረጋግጦ ይፋ የተደረጉትን "መልካም" የማሽላ፣ "ጠረፍ ወርቅ" የአኩሪ አተር፣ "ማርዘነብ" የሰሊጥና "ጃንተከል" የጥጥ ዝርያን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

በተጨማሪም በማዕከሉ የማሽላ፣ ሰሊጥ ፣ አኩሪ አተር፣ የፈረንጅ ሱፍ ፣ ለውዝ ፣ ጤፍና በቆሎ የመነሻ ዘር ብዜት ስራዎች እያካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ጉብኝቱም የጀመረውን ተግባር ለማስፋት የሚያስችል ነው።

በማዕከሉ የሩዝ ሰብል ምርምር ባለሙያ አቶ አሳየ ብርሃኑ እንዳሉት፤ የሩዝ ሰብልን ከፎገራና አካባቢው ባሻገር በምዕራብ ጎንደር ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ስጦታ በመጠቀም ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

 ባለፉት ዓመታት ምርታማነታቸው የተሻሻሉ "ሚሪካ4" እና "አዝመራ" የተሰኙ የሰሊጥ ዝርያዎችን ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ አሁን በሄክታር እስከ 60 ኩንታል የሚሰጥ "ፎገራ1" የተሰኘ ዘር እያባዙ መሆኑን ተናግረዋል። 

የዛሬው ጉብኝትም በዞኑ በሰፋፊ እርሻ ቦታዎች ሩዝን ለማልማት የሚያስችል እየተደረገ ያለውን ጥረት አመራሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገንዝበው እንዲደግፉ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

የመተማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት ፈቃዱ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በምርጥ ዘር ብዜትና አዳዲስ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ ምርታማነት ለማሳደግ ጥረት አድርጓል ነው ያሉት። 

በተለይም በምርምር የተገኘውን "መልካም" የተሰኘ የማሽላ ምርጥ ዘር በማቅረብ ቀደም ሲል በሄክታር ከ16 ኩንታል የነበረውን ምርታማነት ወደ 40 ኩንታል እንዲያድግ ማስቻሉን አውስተዋል።

ወረዳውም ማዕከሉ የምርምር ስራውን ለማስፋፋት እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ለወጭ ንግድና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆን ምርት ለማምረት የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመስክ ጉብኝቱ የተሳተፉት አቶ መስፍን አበራ በበኩላቸው፤ የምርምር ማዕከሉ እያደረገ ያለው የዘር ብዜትና የማላመድ ተግባር በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

 "በማዕከሉ ድጋፍ እየተባዛ ያለው ሰብል ቁመና እጅግ አስደሳች ነው" ያሉት አቶ መስፍን፤ ይህም የምርምር ስራው ውጤታማነትን ያረጋገጠ መሆኑን መመልከታቸውን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም