የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ላይ ግምገማ እያካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በ2017/18 የምርት ዘመን የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የግብርና ግብዓቶች በተሳለጠ መልኩ ተደራሽ መደረጋቸውን በመግለጽ፤ 20 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህም ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና ከመጫወቱም ባለፈ ሀገራዊ የማምረት አቅም እያደገ መምጣቱን አመላካች ነው ብለዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባህል እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፤ ለዚህ ውጤት መገኘት በየደረጃው ያለው የዘርፉ አመራር ቁርጠኝነት ትልቅ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
በሌማት ትሩፋት ኤኒሼቲቭ የወተትና የእንቁላል ምርትን በማሳደግ አመርቂ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ ይህ የተፋስስ ልማትም ለወጣቶች እና ሴቶች ሰፋፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ውጤት የተገኘበት መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 4 ነጥብ 55 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 1 በሊዮን ዶላሩ የተገኘው ከቡና መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በቀጣዩ በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማምጣት ከግብዓት አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተሻለ መልኩ ለመተግበር መረባረብ አለብን ብለዋል።
የዛሬው የግምገማ መድረክም የባለፈው ዓመት አፈጻጸም ላይ በመወያየት ለተሻለ ስኬት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በበጀት አመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 4 ነጥብ 55 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ይታወሳል፡፡