የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ስኬቶች በሚያሳይ መልኩ ይከበራሉ-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ስኬቶች በሚያሳይ መልኩ ይከበራሉ-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እና የተገኙ ሁለንተናዊ ስኬቶችን በሚያሳይ መልኩ እንደሚከበሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ የ2018 የጳጉሜን ቀናት ስያሜዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም የጳጉሜን ቀናት "የኢትዮጵያ ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል እንደሚከበሩ ተናግረዋል።
ጳጉሜን 1 "የእመርታ ቀን" በሚል እንደሚከበር ገልጸው፤ እለቱ ኢትዮጵያ ከአዝጋሚ የእድገት ጉዞ በመውጣት ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የሚዘከሩበት መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው እመርታዊ ለውጦች የሚዘከሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ጳጉሜን 2 "የማንሰራራት ቀን" በሚል እንደሚከበር ገልጸው፤ እለቱ ኢትዮጵያ ወደ ሁለንተናዊ ልማት የተሸጋገረችበትን ጉዞ በሚያሳዩ ሁነቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከጎታች ማነቆ የወጣችበትና ማንሰራራቷም የሚገለጥበት መሆኑን አንስተዋል።
ጳጉሜን 3 "የጽናት ቀን" በሚል እንደሚከበር ገልጸው፤ ታሪካዊ ጽናትን ማስቀጠልን የምናሳይበት ነው ብለዋል። የጽናት ቀን ጀግኖች የሚወሱበትና አዳዲስ ጀግኖች የሚፈጠሩበት መሆኑን ገልጸዋል። በእለቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ የሰንደቅ አላማ የመስቀል መርሀ ግብር እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ጳጉሜን 4 "የህብር ቀን" በሚል እንደሚከበር ገልጸው፤ አንድነትን በሚያጸኑ ተግባራት እንደሚከናወን ገልጸዋል። የትብብር እና የምክክር እሴትን በሚያጎለብቱ ሁነቶች እንደሚከበር ተናግረዋል። በእለቱ ለ150 ሺህ ሰዎች ነጻ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። የስፖርት፣ የተማሪዎች ድጋፍ፣ ማእድ ማጋራት እና ደም ልገሳ በእለቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
ጳጉሜን 5 "የነገ ቀን" በሚል እንደሚከበር ገልጸው፤ የዲጂታል መሰረተ ልማት እና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) መነሻ ባደረጉ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተናግረዋል።