የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያ ስኬቶች እና ፈተናዎችን አልፎ የመሻገር አቅም በሚያሳይ ሁኔታ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያ ስኬቶች እና ፈተናዎችን አልፎ የመሻገር አቅም በሚያሳይ ሁኔታ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያ ስኬቶች እና ፈተናዎችን አልፎ የመሻገር አቅም በሚያሳይ ሁኔታ እንደሚከበር የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ አስታወቁ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ የ2018 የጳጉሜን ቀናት ስያሜዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የጳጉሜን ቀናት ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ትላልቅ ሀገራዊ ስኬቶች እና እመርታዊ ውጤቶች የሚታወሱበትና ህዝቡ እንዲያቃቸው የሚደረግበት መሆኑን አመልክተዋል።
ውስብስብ ፈተናዎችን አልፎ የመሻገር አቅምን ማጠናከር እና ለስኬት ያበቁ ተሞክሮዎችን የሚቀመርበት መሆኑን ተናግረዋል።
የ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያየ ዝግጅትና ስያሜ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ጳጉሜን 1 (የእመርታ ቀን)፣ ጳጉሜን 2 (የማንሰራራት ቀን)፣ ጳጉሜን 3 (የጽናት ቀን)፣ ጳጉሜን 4 (የኅብር ቀን) እንዲሁም ጳጉሜን 5 (የነገ ቀን) በሚሉ ስያሜዎች እንደሚከበር አመልክተዋል።
ቀናቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በመላ ዓለማት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ኮሚኒቲ አባላት እንደሚከበሩ ነው የጠቆሙት።
አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ የጀመረችው የማንሰራራትና የእመርታ ጉዞ ይበልጥ አጠናክራ የምቀጥልበት ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አዲሱ ዓመት የብልጽግና፣ የትብብር እና የትስስር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።