ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ የሚገኘው ኮደርስ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ የሚገኘው ኮደርስ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኮደርስ ስልጠና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለመራመድና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን ስልጠናውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ገለፁ።
የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ ስልጠና ሐምሌ 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
መርሃ ግብሩ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተያዘው ክረምት ወቅት የ5 ሚሊየን የኮደርስ መርሐ ግብር ወደ 7 ሚሊየን ከፍ ለማድረግ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።
የኮደርስ ስልጠናን የተከታተሉ ሰልጣኞች ለኢዜአ እንዳሉት ስልጠናው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮተቤ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ዕፁብ የወንድወሰን ስልጠናን በተመቸ ጊዜ መውሰድ የሚቻልና ከክፍያ ነፃ የሆነ ዕድል መሆኑን ተናግራለች።
ስልጠናው ከዘመኑ ጋር ለመራመድ የሚያስችል ራስን ማብቂያ መንገድ ነውም ብላለች።
በሳውዝ ዌስት አካዳሚ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ነቢዩ ዳዊት፣ ከትምህርት ሰዓቱ ጋር በማጣጣም በቀን ለ30 ደቂቃ ያህል ስልጠናውን በመከታተል ማጠናቀቁን ገልጿል።
ሌሎችም ወጣቶች የኮደርስን ስልጠናን በመውሰድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት እንደ ሀገር የኮደሮችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊየን ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ ነው።
ቀደም ሲል በአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያን ኮደርስ እቅድ ለአዲስ አበባ የተመደበው 809 ሺህ ለማሰልጠን እንደነበርና ሀገራዊ እድቀዱ ወደ ሰባት ሚሊዮን ማደጉን ተከትሎ ወደ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን አንስተዋል።
እስካሁን ባለው ለመመዝገብ ከታቀደው ውስጥ ወደ 985 ሺህ ዜጎች መመዝገባቸውንና ከእነዚህ ውስጥም 871 ሺህ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም የግንዛቤ ስራዎችን በማከናወንና ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ዕቅዱን ለማሳካት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀሪ ጊዜያትም የተማሪዎች ላብራቶሪዎችን፣ የወጣቶች ማዕከላትን፣ ቤተ መጻሕፍትን እና የተለያዩ የማህበረሰብ መድረኮችን በመጠቀም ዕቅዱን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።