በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ጊዜ ሳያባክኑ እድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ጊዜ ሳያባክኑ እድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል
ጎንደር ፤ ነሐሴ 27/2018(ኢዜአ) ፦ በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ጊዜ ሳያባክኑ እድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ በአማራ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።
በጽንፈኛ ቡድኖች የህዝብ ትግል እየተባለ የሚነሳውም ዓላማው ዘረፋና ሃብት የማካበት ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባልም ብለዋል።
በአማራ ክልል በተሳሳተ መንገድ ትጥቅ በማንሳት ጫካ ገብተው የነበሩ ወገኖች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በይቅርታ ወደ ህዝባቸው ገብተዋል፤ እየገቡም ይገኛሉ።
በጎንደርና አካባቢው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ልማት ከገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል አቶ አበበ ሽፈራው፤ ለህዝብ እንታገላለን የሚል ሽፋን በመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ዓላማው ዘረፋ መሆኑን ተረድተናል ብለዋል።
በመሆኑም እራሳቸውና በእርሳቸው ስር የነበሩ ከ50 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን በመያዝ የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ሰላምን መርጠው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ የትኛውም የፖለቲካ ጥያቄ በንግግርና በመግባባት እንደሚፈታ እናምናለን፤ ለዚህም ምቹ እድሎች አሉ የሚሉት አቶ አበበ፤ የትኛውም ታጣቂ ጊዜውን በጫካ ሳያባክን የሰላም እድሉን በአግባቡ ሊጠቀም ይገባዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ህዝብ ከለውጡ በፊት ሆን ተብሎ ብዙ በደሎች ይፈፀሙበት እንደነበር አስታውሰው የመደመር መንግስት ግን የጋራ እሳቤዎችን በመሰነቅ ለሀገር ልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ቆይተንም ቢሆን ተገንዝበናል ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ አቶ ተረፈ እንየው፤ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የትኛውም የትጥቅ ትግል አማራጭ መፍትሄ የማያመጣና የተሳሳተ ስሌት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በጦርነት የሚፈታ የፖለቲካ ጥያቄም ሆነ የሚገነባ ሀገር እንደሌለ ገልጸው በተሳሳተ ቅስቀሳ ወደ ጫካ የገቡ ወገኖቻችን ዛሬ ነገ ሳይሉ የሰላምን አማራጭ በመቀበል ወደ ልማታቸው ሊመለሱ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
በኢትዮጵያ የጠመንጃ ጊዜ አብቅቶ የምክክር ጊዜ እውን መሆኑን በተግባር አይተናል ያሉት የቀድሞ ታጣቂው ከቅራኔ እና ግጭት በመውጣት በልማት ሀገራችንን ለመገንባት መትጋት አለብን ብለዋል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ አቶ ዮሐንስ አዲስ፤ የትጥቅ ትግል ልማትን ከማደናቀፍና ዜጎችን ከማጎሳቆል በስተቀር ሌላ አላማ የሌለውና ውጤት የማያመጣ መሆኑን በትክክል መናገር እችላለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት የተመለከትነው የባእዳንን ተልእኮ ለማሳካት በባንዳነት በመሰለፍ የህዝብን ሃብት መዝረፍና ማውደም ነው ብለዋል ።
በመሆኑም በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች ሁሉ በጥፋታቸው በመጸጸት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል መጥተው ማህበረሰባቸውን መቀላቀልና ወደ ልማት መግባት እንዳለባቸው የቀድሞ ታጣቂዎቹ መክረዋል።