ቀጥታ፡

በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ)፦በአዲሱ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት ቀድመው መሰራታቸውን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በትምህርት ዘመኑ ከ13 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል።

በክልሉ በሚገኙ 37 ሺህ 127 ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

የቢሮው ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥በአዲሱ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት ቀድመው ተሰርተዋል።

በዘንድሮው ዓመት በማህበረሰቡ ተሳትፎ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት 1ሺህ 597 የቅድመ መደበኛ፣ 284 የ1ኛ ደረጃ እና 23 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በርካታ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እንደ አዲስ መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

በሕፃናት ተማሪዎች ላይ ጠንካራ መሠረት በመጣል ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድን ለማፍራት ታቅዶ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ለአብነትም 695 የቅድመ መደበኛ እና 728 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሞዴል ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

በክልሉ በገጠር አካባቢዎች 19 ሺህ 752 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን የጠቀሱት ዶክተር ቶላ፤ የመምህራንን አቅም ለማጎልበትም የተለያዩ አጫጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ዓመት ከ20 ሚሊዮን 600 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛና የ1ኛ ደረጃ መጻሕፍት ታትመው መዘጋጀታቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ እስካሁን 2 ሚሊዮን የሚሆኑት ለትምህርት ቤቶች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ እውቀት ለማሳደግ የሚያስችሉ 117 የዲጂታል ፓርክ፣ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ ሙከራዎች መዘጋጀታቸውንም አክለዋል።

በተለይም ትምህርት ቤቶች ያላቸውን መሬት በአትክልት፣ ፍራፍሬና እንስሳት እርባታ በማልማት ለተማሪዎች ምገባ መርሃግብር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በራሳቸውን እንዲሸፍኑ የሚያስችል እንቅስቃሴ መደረጉን ተናግረዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ጎልማሶችን ጨምሮ ወደ 6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ለተሸጋገሩ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ካሳሁን ገላና (ዶ/ር) በበኩላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በ'ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ' አማካኝነት ለተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት አሠራሩን በማዘመንና በተሻለ ደረጃ በማደራጀት መርሃ ግብሩን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት በክልሉ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞች ተማሪዎችን ለመደገፍ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኞች የደንብ ልብስ፣ ደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን እያቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ በ2019 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ ከመስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም የሚጀመር መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም