ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ የሚመራበት የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ ለሚታዩት ለውጦች ዋነኛ መሠረት ናቸው

አዲስ አበ ፤ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ) :-ብልፅግና ፓርቲ የሚመራበት የመደመር እሳቤና የፓርቲው ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ለሚታዩት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ዋነኛ መሠረት መሆናቸውን በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ነብዩ ስሑል ገልጸዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅ/ቤት የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ነብዩ ስሑል የተመራ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ልዑክ በቻይና ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።

ልዑኩ በቤጂንግ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ ጋር የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ አቶ ነብዩ ስሑል፣ ብልፅግና ፓርቲ የሚመራበት የመደመር እሳቤና የፓርቲው ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ለሚታዩት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ዋነኛ መሠረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲው ውጤታማነት፣ የከተማና የገጠር ልማትን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን፣ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እና የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የፓርቲውን የእሳቤ ጥራትና የማስፈጸም አቅም የሚያሳዩ ዋነኛ ተግባራት መሆናቸውንም አቶ ነብዩ ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከሀገር ውስጥ የልማት ሥራ ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም እያጠናከረ ያለ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

በፖለቲካው መስክ እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ለውጦችን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ በ2026 የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ መመረጧንና ለጉባኤው ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አስረድተዋል።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል  ሪኦ ዩሃ ብልፅግና ፓርቲ “ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግሥት፤ ጠንካራ መንግሥት ለጠንካራ ሀገር” በሚል እሳቤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እያስመዘገበ ያለውን ለውጥ  ፓርቲያቸውና መንግሥታቸው በከፍተኛ አድናቆት እንደሚከታተሉ ገልጸዋል።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲና ብልፅግና ፓርቲ በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት የሚያደርጉትን ትብብር እና የጋራ ጥቅሞችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት በቀጣይ ለማጠናከር ፓርቲያቸው ጠንካራ አቋም እንዳለው አረጋግጠዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ልዑክ በቤጂንግ በነበረው የመጀመሪያ ቀን ውሎ፣ ከሁለትዮሽ ውይይቱ በተጨማሪ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን ታሪክ፣ ልምድ፣ ድሎችና ተግዳሮቶች የሚያሳየውን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሙዚየም መጎብኘቱን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም