ለሀገር ታማኝ ሆኖ መስራትና ልማትን መደገፍ የሚያኮራ ተግባር ነው- ተሸላሚ ግብር ከፋዮች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ታማኝ ሆኖ መስራትና ልማትን መደገፍ የሚያኮራ ተግባር ነው- ተሸላሚ ግብር ከፋዮች
አሶሳ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፡- ለሀገር ታማኝ ሆኖ መስራትና ልማትን መደገፍ የሚያኮራ ተግባር መሆኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሸላሚ የሆኑ ግብር ከፋዮች ገለጹ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ለታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሽልማትና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
ከታማኝ ግብር ከፋዮች መካከል አቶ ሙፍቲ ሀሊፋ፤ ግብርን በታማኝነት መክፈል ለሀገር ልማትና ለዜጎች አገልግሎት ታማኝ ሆኖ መገኘት መሆኑን ገልጸዋል።
በወርቅ ማእድን ስራ ላይ የተሰማሩትና በበጀት ዓመቱ ከ37 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ የከፈሉት አቶ ሙፍቲ፤ የክልሉን ልማት ለማፋጠንና ለዜጎች ተጠቃሚነት በመስራታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ሌሎችም በታማኝነት ግብር ሲከፍሉ ለራሳቸው፣ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ታማኝ መሆናቸውን እያስመሰከሩ መሆኑን አንስተው በዚሁ መቀጠል አለብን ብለዋል።
ሌላኛው ታማኝ ግብር ከፋይና ተሸላሚ አቶ እዮብ ዲታሞ፤ ግብይትን በደረሰኝ ብቻ መፈጸም ወጪና ገቢን በቀላሉ ከመለየት በተጨማሪ ግብራቸውን በመረጃ ለመክፈል እንዳገዛቸው ገልጸዋል።
ድርጅታቸው ለተከታታይ ዓመታት ታማኝ ግብር ከፋይ በመሆን እውቅና እና ሽልማት ማግኘቱን አስታውሰው፤ በቀጣይም በታማኝነታችን ለሀገራችን የምናደርገውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ሌላኛው ተሸላሚ የሆኑት አቶ መብራቱ የኋላ፤ የግብር መክፈል ጉዳይ ለሀገር እና ለዜጎች ተጠቃሚነት በመሆኑ ሁላችንም የዜግነት ግደታችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ለሀገር ታማኝ ሆኖ መስራትና ልማትን መደገፍ የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ያነሱት ግብር ከፋዮቹ በዚሁ ተግባራቸው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የታደሙ ታማኝ ግብር ከፋዮች ከምስጋና ጭምር የሚዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።