ቀጥታ፡

በዲላ ከተማ የተከናወኑ ልማቶች የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች እየመለሱ መጥተዋል - የከተማው ምክር ቤት አባላት

ዲላ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፡-በዲላ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የሕዝብን ጥያቄዎች እየመለሱ በመምጣታቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው  የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

አባላቱ በዲላ ከተማ የተከናወኑና በሂደት ላይ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በአባላቱ ምልከታ ከተደረገባቸው የልማት ስራዎች መካከል ለተጠቃሚዎች የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት፣ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ፣ የዲላ መሶብ አንድ ማዕከል የአገልገሎት መስጫ ይገኙበታል።


 

የልማት ፕሮጀክቶቹ በምክር ቤት ከአባላት በተደጋጋሚ ለሚነሱ የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ መሆናቸውንም አባላቱ ተናግረዋል። 

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ አበራሽ ወራሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማ አስተዳደሩ ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች አመላካች ናቸው።

በተለይ የአስፓልት መንገድን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የኮሪደር ልማትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት የሚበረታቱና በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው ብለዋል።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲላ ከተማ እየታየ ያለው ፈጣን የልማት ጉዞ ተስፋ የሚሰጥ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ መሐመድ ጉሚ ናቸው።

የልማት ሥራዎቹ የከተማዋን ነዋሪ የልማት ጥያቄዎች ከመመለስና የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር አንጻር ጉልህ አስተዋጾ እያደረጉ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በከተማው የህዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በሚከናወኑ ተግባራት እንደ ምክር ቤት አባልነታቸው ህዝብን በማስተባበርና አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አስተዋጾ ማድርጋቸውንም ጠቁመዋል።

ወይዘሮ መሠረት በየነ የተባሉ ሌላው አባል በበኩላቸው፣ በከተማው የተከናወኑ የልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታና ደረጃ እየቀየሩ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።

ልማቱ የበርካቶችን ሕይወት ያቀናና የሥራ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር ከነዋሪው ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ መሆኑ ተናግረዋል።

ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልገሎትን ጨምሮ የዲጀታል አሰራርን በተለያዩ ሴክተር ተቋማት ተግባራዊ ማድረጉንም አመልክተዋል። 

ይህም የከተማዋን እድገት ከማፋጠን ባለፈ ለነዋሪዎቿ የተሻለ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም