ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ አርሶ አደሩን ወደ ኢንቨስተርነት የማሸጋገር ስራ ውጤት እያመጣ ነው

ሸገር ፤ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ አርሶ አደሩን ከባህላዊ የአሰራር ዘይቤ በማላቀቅ ወደ ኢንቨስተርነት የማሸጋገር ስራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ጉዬ ገለጹ።

የሸገር ከተማ የገበሬዎች ቀን «ዘመናዊ ገበሬና ዘመናዊ ግብርና ለአጠቃላይ ብልፅግና» በሚል መሪ ቃል በከተማው ሱሉልታ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ይገኛል። 

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግም የባዛር እና ኤግዚቢሽን መርሃ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የግብርና ምርቶች፣ የግብርና ማሽነሪዎችና ግብዓቶች  ለእይታ ቀርበዋል።


 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ጉዬ፤ ሸገር በጥቂት ዓመታት ቆይታ ውስጥ ታላላቅ ስኬቶችን እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸዋል።

የሸገር ከተማ ከተመሰረተች በኋላ በተለይም በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮችን የግብርና ቴክኖሎጂዎች፣ የግብዓት አቅርቦት፣ ሙያዊ ድጋፍና መሰል ጉዳዮችን በማቅረብ ውጤታማ እንዲሆኑ በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ እንዳለ አመልክተዋል።

በመሆኑም በከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደሩን ከባህላዊ የአሰራር ዘይቤ በማላቀቅ ወደ ኢንቨስተርነት የማሸጋገር ስራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል። 

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በበኩላቸው በመደመር  እሳቤ ባለፉት ዓመታት ከተማዋን የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ከተከናወኑት ተግባራት ጎን ለጎን የአርሶ አደሩንና የከተማዋን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

ከተማው የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ አቅም በመገንባትና በማሳደግ በጋራ የምታድግ ከተማ መሆኗንም ገልጸዋል።


 

የእርሻ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂን በማስፋት፣ የግብርና ግብአቶችን በወቅቱ በማቅረብ እንዲሁም የአርሶ አደሩን የሥራ ባህል በመለወጥ በርካታ አርሶ አደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት ማሸጋገር መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል።

እንዲሁም የንግድ ቦታዎችንና የተለያዩ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ በርከታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በከተማው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ አቶ ግርማ ሀይሉ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ቀደም ሲል ከመሬቱ ይፈናቀል የነበረው አርሶ አደር አሁን በመሬቱ ላይ ባለቤት ሆኖ በተለያዩ ዘርፎች በመደራጀት ምርትና ምርታማነቱን እያሳደገ ይገኛል።


 

በመደመር መንግስት ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን መታደግ መቻሉንም አንስተዋል።

በዚህም አርሶ አደሩንና ግብርናውን በማዘመን የከተማዋን የዕድገት ጉዞ ለማሳደግና አጠቃላይ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የዛሬው መርሃግብር  ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም