ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ እመርታ የአዲሱ ትውልድ ታሪካዊ የልማት ውርሶች ናቸው - አረጋውያን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ የልማት እመርታ ዘመናዊ ከተሜነትን የፈጠሩ የአዲሱ ትውልድ ታሪካዊ የልማት ውርሶች መሆናቸውን አረጋውያን ገለጹ።  

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን የአረጋውያን የከተማ ቱሪዝምና ተሳትፎ የጉብኝት መርሃ ግብር አካሂዷል።

በጉብኝት መርሃ ግብሩ የተሳተፉ አረጋውያን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ የልማት እመርታ ዘመናዊ ከተሜነትን የፈጠሩ የአዲሱ ትውልድ ታሪካዊ የልማት ውርሶች ናቸው ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ አስራት ሞገስ፤ የመዲናዋ ዘመናዊ የመስህብ መዳረሻ የልማት ስኬቶች አዲሱ ትውልድ ከታሪክ ነጋሪነት ወደ ታሪክ ሰሪነት መሸጋገሩን ያበሰሩ ናቸው ብለዋል።

አዲስ አበባን ዘመናዊ የከተሜነት ምኅዳር ያላበሷት የልማት ውጤቶችም አንድነትና ትብብርን በማጠናከር የሀገርን ዕድገት ማፋጠን እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ መኮንን ደለሌ በበኩላቸው፤ የመዲናዋ የልማት ውጤቶች የመጪው ትውልድ የሚዘክራቸው የአዲሱ ትውልድ የታሪክና ቅርስ አሻራ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎችም የአዲስ አበባን ውብና ማራኪ የልማት ውጤቶች ጠብቆና ተንከባክቦ በመጠቀም ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የልማት ውጤቶቹም የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሀገርን የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞ በመደገፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አብራርተዋል።


 

የኮሚሽኑ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ቡድን መሪ አቶ አማኑኤል ባቡ በዚህ ወቅት፤ የመዲናዋ የቱሪዝም ልማት ውጤቶች የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው ብለዋል።

የመዳረሻ ልማት ውጤቶችም የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በማጽናትና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ልማትን በማሳለጥ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጉብኝቱ ዓላማም አረጋውያን ለሀገራቸው የከፈሉት ውድ ዋጋ በአዲሱ ትውልድ ቅብብሎሽ በእመርታዊ የልማት ጉዞ እየቀጠለ እንደሚገኝ ለማስገንዘብ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ወታደራዊ ቅርስና ሙዚየም ማዕከል የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል አግዘው ባልታየው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ቅድመ አያቶች በከፈሉት ውድ ዋጋ በትውልድ ቅብብሎሽ እየተገነባች የምትገኝ ሀገር ናት።


 

ማዕከሉን የጎበኙት አረጋውያንም በሕይወት ዘመናቸው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በተለያየ መስክ በማገልገል አሻራቸውን ያሳረፉ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ባለውለታ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአረጋውያን ልብና አእምሮ ያተሙ የታሪክ ማስታወሻዎች ለልጅና ለልጅ ልጆቻቸው የሚተላለፉ የክብር አስተምህሮዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

የአረጋውያኑ የማዕከሉ ጉብኝትም ያለፈውን ታሪክ እንዲያስታውሱና የአሁኑ ትውልድም የራሱን ታሪክ እየጻፈ መሆኑን ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም