ኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች እሴት በተጨመረበት የቡና ምርት ላይ እንዲሳተፉ ትፈልጋለች - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች እሴት በተጨመረበት የቡና ምርት ላይ እንዲሳተፉ ትፈልጋለች - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም በመጠቀም፣ የቻይና ባለሃብቶች እሴት የሚጨምሩ የቡና ኢንዱስትሪዎችን በሀገሪቱ ውስጥ እንዲገነቡ ፍላጎት መኖሩን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዝናቡ ይርጋ ገለጹ።
“2026 የዩናን-ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ንግድና የቡና ኢኮኖሚ ትብብር ማስተዋወቂያ ጉባኤ” በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዝናቡ ይርጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት ላይ እንዲሳተፉ ፍላጎት አላት።
ለዚህም ኢትዮጵያ ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት ጠቅሰው የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እሴት የሚጨምሩ የቡና ኢንዱስትሪዎችን እንዲገነቡ ፍላጎት መኖሩን አብራርተዋል።
የቻይና ባለሀብቶች በቡና ምርት፣ በዘመናዊ ማቀነባበሪያ፣ ከምርት ጀምሮ ለገበያ እስከሚቀርብ ባለው ሂደት የዲጂታል ክትትል መስኮች ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም የግብርና ሥርዓት መኖሩ ሌላው ምቹ ሁኔታ መሆኑን አንስተው፤ በዘመናዊ ማሸጊያ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መኖሩንም አብራርተዋል።
የቻይናዋ ዩናን ግዛት የንግድ መምሪያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሊ ዪ በበኩላቸው፤ በዩናንና ኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ በእጥፍ እያደገ መምጣቱን አሳውቀዋል።
የዩናን ግዛት በዚህ የንግድ ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ 20 የቡና ኩባንያዎችን ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ትኩረታቸውም ከኢትዮጵያ ጥራት ያለው አረንጓዴ ቡና ግዥና ንግድን ማስፋት መሆኑን ገልጸዋል።
ዩናን በቻይና የቡና ኢንዱስትሪ ዋና ማዕከል እንደሆነች ጠቅሰው፣ ትላልቅ ቡና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ የተስፋፉባት መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ከኢትዮጵያ የሚገኘውን ጥራት ያለው ጥሬ ቡና በዩናን በማቀነባበር እሴት ጨምሮ ወደ ቻይናና ዓለም ገበያ ለማቅረብ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና ንግድ ካውንስለር ሊዩ ሺያኦጓንግ በበኩላቸው፤ ቻይና የኢትዮጵያ ትልቋ የንግድ አጋርና የኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን ገልጸዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ ምርቶች የዜሮ ታሪፍ የገበያ ዕድልን ጨምሮ የንግድ ማመቻቸት ሥርዓቶችን በማስፋት የኢትዮጵያ ምርቶች በቻይና ገበያ ተደራሽ እንዲሆኑ እየሠራች መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የዩናን ግዛት እና ኢትዮጵያ በአየር ንብረትና በጂኦግራፊ ተመሳሳይ ባህሪያት ያላቸው መሆኑን አመልክተው፤ በቡና ዘርፍ የጋራ ትብብር ለማስፋት የተሻለ መሠረት መፍጠሩን ገልጸዋል።
የቻይና ገበያ በተለይም ለከፍተኛ ጥራት ያለው የቡና ጥሬ ዕቃ ፍላጎቱ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ የሚገኘውን ልዩ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡና ወደ ዩናን በማስገባት በማቀነባበርና በማስተዋወቅ የገበያ እሴቱን ለማሳደግ ፍላጎት መኖሩን አስረድተዋል።
እንደ ካውንስለሩ ገለጻ፣ ይህ ትብብር በቡና ንግድ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንዱስትሪ ልማት ዕድሎችንም የሚያሰፋ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያና የዩናን የንግድና ኢንቨስትመንት ተወካዮች የቡና ንግድን፣ የገበያ ትስስርንና የጋራ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስፋት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።