ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፎረምና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ይካሄዳል - የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግርና ዘላቂ የኢንቨስትመንት እድል የሚያሰፋ የመጀመሪያው የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፎረምና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስታውቀ።

የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ ካሳሁን ማሞ፤ ምክር ቤቱ ከኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀውን የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፎረምና ኤግዚቢሽን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የኢትዮጵያን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካትና ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

ፎረምና ኤግዚቢሽኑም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የአረንጓዴ ቢዝነስ ኩባንያዎችና አልሚዎች በተሳተፉበት ጳጉሜን 3 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማላቅ ዘላቂ ሥነ-ምህዳራዊ ዕይታን ያማከለ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት እንዲጎለብት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ረገድ ከጀርመን ዓለም አቀፍ የትብብር ድርጅት እና ከኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር የአረንጓዴ ልማትና ዘላቂነት ማዕከል ማቋቋሙን አመልክተዋል።

የአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ፎረምና ኤግዚቢሽንም ጤናማ ሥነ-ምኅዳርን የተከተለ የታዳሽ ኃይልና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በማጠናከር የዘርፉ ተዋናዮች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

መድረኩም በአረንጓዴ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን፣ የፋይናንስ ተቋማትንና ሥራ ፈጣሪዎችን በማገናኘት አዳዲስ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር በማፋጠን ዘላቂ ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋትና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማላቅም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል።


 

በኔዘርላንድ የልማት ድርጅት የሊዌይ የፕሮግራም ማኔጀር ሔለን ጌታው በበኩላቸው፤ መድረኩ ከአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ነው ብለዋል።

ፎረሙም በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎችን የፋይናንስ፣ የገበያ፣ የቴክኖሎጂና የመረጃ ተግዳሮቶች በመለየት መፍትሔ የሚመላከትበት ጠቃሚ መድረክ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት የገበያ ትስስርና የድጋፍ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም