ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት መፍጠርና ማሰናሰል የሚችል ትውልድ ለመገንባት መሠረት እየጣለ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ በማሳደግ መፍጠርና ማሰናሰል የሚችል ትውልድ መገንባት የሚያስችል መሰረት እየተጣለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

33ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ “ብሩህ ነገን በዛሬ አዕምሮዎች” በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።


 

ጉባኤው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ በመማር ማስተማር ሂደት የተከናወኑ ጠንካራ ሥራዎችን በመገምገም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተከናወነው ተግባር የተማሪዎች ውጤት መሻሻሉንና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች የማለፍ ምጣኔ ወደ 33 በመቶ ማደጉ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ በጀት በመመደብ፣ በቀዳማይ ልጅነት፣ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትውልድን በዕውቀትና በሥነ ምግባር ለማነጽ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የትምህርት ዘመን በርካታ ውጤቶች የተገኙበትና ለሌሎችም አርዓያ የሚሆኑ ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የ6ኛና 8ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገበው ውጤት ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ትልቅ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።

በተለይም በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በተሠሩ ጠንካራ ሥራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተው፣ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመትም እንደ ከተማ 33 በመቶ ማሳለፍ መቻሉን በመግለጽ፣ ይህንንም በቀጣይ ማሻሻል እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጉባኤው ዓላማ በ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የተመዘገቡ ውጤቶችን በመገምገም በቀጣይ ይበልጥ የተሻለ ሥራ እንድንሠራ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የትምህርት ዓመቱ በርካታ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን በመግለጽ፤ በተለይም የትምህርት ቤት ደረጃን በማሻሻል የተማሪዎች ውጤት የተሻሻለበት ዓመት መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ፈተና ተፈታኞችና ትምህርት ቤቶች የእውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከግል ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል የላቀ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪዋ ከሴቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ሪና አዱልከሪም እንዳለችው፤ በፕሮግራም በመመራትና በማጥናት ከፍተኛ ውጤት አምጥታለች።

ሌላው ከመንግሥት ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል የልዩ ፍላጎት ተማሪ የሆነውና ከፍተኛ ውጤት ያመጣው ተማሪ ሚካኤል ደረጀ በበኩሉ፣ የአጠናን ስልቴን በፕሮግራም በመምራት ከፍተኛ ውጤት አምጥቻለሁ ብሏል።

በውጤታማ አጠናንና በትምህርት ቤት የማጠናከሪያ ትምህርት በመከታተል የተሻለ ውጤት አምጥቻለሁ ያለችው ደግሞ ከመንግሥት ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ ሲንግተን ሀይሉ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም