ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ የቼልሲውን ኤንዞ ፈርናንዴዝን ለማስፈረም ተስማማ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ ማንችስተር ሲቲ በዝውውር መስኮቱ ማብቂያ ቀን የቼልሲውን አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝን በ125 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

የ25 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አማካይ ከቤንፊካ በ107 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ቼልሲ የተቀላቀለው እ.አ.አ በ2023 ነበር።

ተጫዋቹ ቼልሲ ከፉልሃም ጋር ባደረገው የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ከሉተን ጋር በካራባኦ ካፕ እንዲሁም ከብራይተን ጋር በተደረገው የሊጉ መርሐ ግብር አልተጫወተም።

ይህ ዝውውር ሊቨርፑል ባለፈው ዓመት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ማጠናቀቂያ ቀን የኒውካስትል ዩናይትዱን አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳክ ለማስፈረም ከከፈለው የእንግሊዝ ክብረ ወሰን ክፍያ እኩል መሆኑን ስካይ ስፖርትስ ዘግቧል።

ፈርናንዴዝ ወደ ማንችስተር ሲቲ ማምራት እንደሚፈልግ ያሳወቀ ሲሆን፣ በኢትሃድ ከቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኙ ኤንዞ ማሬስካ ጋር እንደገና ይገናኛል።

ተጫዋቹ በቀጣይ ሰዓታት ውስጥ የሕክምና ምርመራዎችን አድርጎ ዝውውሩን ሙሉ በሙሉ ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ቼልሲ አርጀንቲናውን አማካይ የሚተካ ሌላ ተጫዋች ለማስፈረም እየሰሩ ይገኛሉ።

ክለቡ የሮማውን ማኑ ኮኔ እና የሞናኮውን ላሚን ካማራን ለመግዛት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ የሚገኙ ሌሎች አማካዮችንም እየተመለከተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም