በሶማሌ ክልል የመማር ማስተማር ስራውን በቅንጅት በመምራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የመማር ማስተማር ስራውን በቅንጅት በመምራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
ጅግጅጋ፣ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የመማር ማስተማር ስራን በቅንጅት በመምራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2019 የትምህርት ዘመን ዝግጅትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጠይብ ሙሀሙድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት፣ የመምህራን አቅም በመገንባት እና የግብአት አቅርቦትን በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን አስጠብቆ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የትምህርት ቤቶችን ምድረ ግቢ ሳቢ የማድረግና የእድሳት ስራ መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የመማር ማስተማር ስራውን ለማሳካት ከሚደረገው ዝግጅት በተጓዳኝ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይቀሩ ንቅናቄ እየተካሔደ መሆኑን ገልፀዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመንም ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማስገባት በሚደረገው ንቅናቄም የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በቅንጅት እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ በ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩን ሂደት በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ተማሪዎች በቁሳቁስ እጥረት ከትምህርታቸው እንዳይቀሩም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ20 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ የ2019 የትምህርት ዘመን መስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም የሚጀመር መሆኑን ገልጸው፣ ወላጆች እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት በማምጣት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።