በጅማ ዞን ከ180 በላይ አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ ይሆናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን ከ180 በላይ አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ ይሆናሉ
ጅማ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ) ፡-በጅማ ዞን ከ180 በላይ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለመጪው አዲስ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንደሚሆኑ ተገለጸ።
የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ለጠቅላላው የትምህርት ሥርዓት ጥራት፣ ውጤታማነት እና ስኬት የመሠረት ድንጋይ ነው።
የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ህጻናት መደበኛ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የፊደላት፣ የቁጥሮች፣ የቅርፆች እና የመሠረታዊ ቃላት እውቀት እንዲጨብጡ ያደርጋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም የትምህርት ጥራትን ከሥሩ ለማረጋገጥ እና የሕፃናትን አእምሯዊ ዕድገት ለማፋጠን የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት በመጨመር ረገድ በርካታ አዎንታዊ ተግባራትን አከናውኗል።
በጅማ ዞንም የቅድመ-መደበኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በተደረገው እንቅስቃሴ በዘንድሮው ዓመት የ184 አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የገለጸው።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሚፍታህ አብዱልቃድር እንደገለጹት፣ ትምህርት ቤቶቹ በመንግሥት በጀትና በሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ እየተገነቡ የሚገኙ ሲሆን፣ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ለበርካታ ሕፃናት የትምህርት ዕድል የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል።
ትምህርት ቤቶቹ በአጭር ቀናት ውስጥ ተጠናቀው ለመማር-ማስተማር ሥራ ዝግጁ እንደሚደረጉም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
ከቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ 24 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታም በተመሳሳይ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ሚፍታህ አክለውም፣ ነባር ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋትና ለማደስ በተደረገው ጥረትም 750 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የትምህርት አሰጣጡን ጥራት ለማሻሻልና ሕፃናት ከታች ጀምሮ ጠንካራ የእውቀት መሠረት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ ለመምህራንም ልዩ ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመጻሕፍት እጥረት ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚያስተምሩ 5 ሺህ መምህራን ሥልጠና መሰጠቱን እና የሚስተዋለውን የመጻሕፍት እጥረት ለመቅረፍ ከ16 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትን ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።