ከውስጣዊ ዐቅም ትንሣኤ እስከ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት፡ የኢትዮጵያ የጽናት ምዕራፍ! - ኢዜአ አማርኛ
ከውስጣዊ ዐቅም ትንሣኤ እስከ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት፡ የኢትዮጵያ የጽናት ምዕራፍ!
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎችን በጽናት በመመከት፣ ፈተናን ወደ ታሪካዊ ዕድል መቀየር የሚቻለው በውስጣዊ ዐቅም ልዕልና እንጂ በውጭ ጥገኝነት እንዳልሆነ በተግባር አሳይታለች።
መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የነደፋቸው የልማት እና የሪፎርም ማዕቀፎች ሀገሪቱን ከውጭ ተጽዕኖዎች በሂደት በማላቀቅ፣ በማንኛውም ፈተና ውስጥ የማይበገር ሁሉን አቀፍ ሉዓላዊነት እንዲገነባ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
በግብርናው ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ምርታማነትን እና የዝናብ ጥገኝነትን በማሻሻል የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን የተረጂነት ታሪክ በመስበር የምግብ ሉዓላዊነትን ወደሚያረጋግጥ ዐዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በክላስተር ግብርና እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተመዘገበው እመርታ ከውጭ በሚገባ የስንዴ ዕርዳታ ላይ የተመረኮዘውን የሀገራችንን እውነታ ቀይሮ፣ በሀገር ውስጥ ምርት ራስን ከመቻል አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የተረፈ ምርትን ማቅረብ ያስቻለ ተጨባጭ ውጤት አሳይቷል።
የአምራች ኢንዱስትሪ የማምረት ዐቅምን እና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሻሻል፣ የማዕድን ምርት ጥራት እና እሴትን በመጨመር፣ የውጭ ዕዳ ጫናን በመቀነስ እና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ገበያ በመፈጠር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን በማረጋገጥ፣ የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር እመርታዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
እንደ ለሚ ኩራ እና ቂሊንጦ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የቴክኖሎጂ ሽግግርን እያረጋገጡ ይገኛሉ። የሲሚንቶ፣ የብረታብረት እና የኬሚካል ምርቶች የሀገር ውስጥ ፍላጎት በብቃት እንዲሸፈን ተደርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ወርቅ እና ታንታለም ያሉ ወሳኝ ማዕድናትን ከጥሬ ዕቃ ንግድ አሠራር ወጥተው በሀገር ውስጥ እንዲጣሩ እና እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ውጭ እንዲላኩ የተደረገው ጥረት የኢኮኖሚ ጽናታችንን አጠናክሯል።
የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ፖሊሲ እና የታክስ ማሻሻያዎች ሀገራዊ ዐቅምን እያጎለበቱ፣ የበጀት ነፃነታችንን እያረጋገጡ ቀጥለዋል።
በዲጂታል፣ በኢነርጂ፣ በሰው ሀብት ልማት እና በጤና መስኮች የተሠሩ ሰፋፊ ማሻሻያዎች በቴክኖሎጂ፣ በኃይል እና በሕክምና ግብዓት አቅርቦት ራስን የምትችልበትን ዐቅም ፈጥረዋል።
እንደ "ፋይዳ" ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዐት እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዐት የዜጎችን ዳታ ከውጭ ተቋማት ሞግዚትነት ነፃ አውጥተዋል። የቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል ፓርክ እና ሌሎች የሀገር ውስጥ መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች መሠረታዊ መድኃኒቶችን፣ የሕክምና ኦክስጅን እና የክትባት አቅርቦቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ ይገባ የነበረዉን በማስቀረት በጤና ዘርፍሉ አስቻይ የሉዓለዊነት ዐቅም ፈጥረዋል።
ከዚህ ባለፈም የወጣቶችን ፈጠራ ሥነ-ምኅዳር እና የዲጂታል ክሕሎት ማሳደግ የሚያስችሉ የስታርት-አፕ ሥራዎች የውስጣዊ ዐቅማችን ማዕቀፍ አካል ሆነዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የኃይል አቅርቦት ዐቅማን በማሳደግ ቀጣናዊ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ማድረግ አስቸለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን በመቋቋም ተምሳሌት መሆን ተችሏል።
በዲፕሎማሲ እና በጂኦ-ፖለቲካ ዓውድም ሀገሪቱ በብሪክስ (BRICS) አባልነት፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች የጋራ ተጠቃሚነትን እና ነጻ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን በማስቀደም የሉዓላዊነት ዐቋሟን አጠናክራለች።
የኢትዮጵያ የፀጥታ ተቋማትና የመከላከያ ሠራዊት የገነባው የላቀ ወታደራዊ ዐቅም እና በራስ የማምረት ውስጣዊ ዐቅምም የመቻላችን ምስክር ከመሆን ባለፈ የሀገራዊ ክብር መገለጫ ሆኗል።
የእነዚህ ስኬቶች እውነተኛ ባለቤት የሆነው ሕዝባችን ዛሬ ላይ በመደመር መንግሥት መሪነት የዘመናት የተረጂነት አስተሳሰብን ሰብሮ በመውጣት በሁሉም መስክ ዐዲስ ታሪክ መጻፍ ጀምሯል።