በምስራቅ ቦረና ዞን ቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር በበልግ ወቅት የለማው ምርት ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን ቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር በበልግ ወቅት የለማው ምርት ተሰብስቧል
ነገሌ ቦረና ፤ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ቦረና ዞን ቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር በዘንድሮ በልግ አዝመራ ከለማው መሬት ከሰባት ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ቡሳ ጎኖፋ በኦሮሚያ ክልል በተለያየ ምክንያት ለችግር ለሚጋለጡ ወገኖች ፈጣንና ዘላቂ ድጋፍ ለመስጠት፣ የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ እንዲሁም ህብረተሰቡ እርስ በእርስ የሚረዳዳበትን ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ማዕከል በማድረግ የተዋቀረ ተቋም ነው።
በተለይም በክልሉ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች በተደጋጋሚ በሚከሰቱባቸው እንደ ምስራቅ ቦረና ባሉ አካባቢዎች ተቋሙ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና አደጋዎችን በራስ አቅም ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዞኑ በበልግ አዝመራ ከለማው መሬት የተሰበሰበው ከሰባት ሺህ ኩንታል በላይ ምርትም የቡሳ ጎኖፋን የምግብ እህል ክምችት ከማጠናከሩ ባሻገር፣ ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የምስራቅ ቦረና ዞን ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዋሪዎ ሀሰን ለኢዜአ እንዳስታወቁት ጽህፈት ቤቱ በዞኑ ለሚከሰቱ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተለያዩ አካባቢዎች ሰብሎችን የማምረት እንቅስቃሴ ውሰጥ ገብቷል።
በዚህ ረገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በዞኑ በዘንድሮ የበልግ አዝመራ በ172 ሄክታር መሬት ላይ ካለማው ስንዴ፣ ጤፍና በቆሎ 7 ሺህ 130 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የሰብል ልማቱ ቡሳ ጎኖፋ ራሱን ችሎ ለማልማት እየተንቀሳቀሰ እንዳለና ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ምስራቅ ቦረና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ ቆለማና ዝናብ አጠር በመሆኑ አብዛኛው የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በእንስሳት እርባታና ውጤቶቹ እንደሚተዳደር አስታውሰዋል።
በመሆኑም የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከዘንድሮ ሰብል ልማት ልምድና ተሞክሮ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ሰውሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም በዞኑ ከ481 ሺህ በላይ አባላት ማፍራት መቻሉንም አክለዋል።
በተያዘው በጀት አመት ከ179 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ድርቅና መሰል ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም ወደ ስራ መገባቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም እስካሁን ድረስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአባላትና ደጋፊዎቹ ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡንም አክለዋል።
ከአባላቱ መካከል የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ አቶ ነጋሽ ሀይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በራስ አቅም ችግሮችን ለመቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታና የሚደግፉት ነው።
ካለፈው አመት ጀምሮ እስካሁን የጉልበትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል።
የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ገመቹ ገቢሳ በበኩላቸው ቡሳ ጎኖፋ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጠናክር በጎ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ አደጋ ባጋጠመ ቁጥር ከእርዳታ ጠባቂነት በመላቀቅ በራስ እቅም ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።