ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት መሠረት ይጥላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የሚጥል መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ አደረጃጀቶች፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት አጀንዳዎች በመምከር ችግሮችን በንግግር መፍታት የሚቻልበትን አዲስ የታሪክ አሻራ አስቀምጦ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ያካሄደችው አካታችና አሳታፊ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የሕዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክር፣ ሀገራዊ መነሳትና የዕድገት ዘመንን የሚያበስር ታሪካዊ ክስተት ነው።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፣ የምክክር ጉባዔው በኢትዮጵያ ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት የሰለጠነ ማኅበረሰብ ባህልን ያንጸባረቀ ነው።

በኢትዮጵያ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የተዘራውን የጥላቻ ትርክት በማረቅ፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትንና የእኩልነት እሴቶችን ማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ በታሪክ ሲወሳ የሚኖር አኩሪ የትውልዱ አሻራ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የሀሳብ ልዩነቶችን በማጥበብ አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት ምክክር ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያውያን የምክክር ጉባዔውን ተጠቅመው ለሀገራቸው በሚበጁ ጉዳዮች ላይ ተመካክረው የጋራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማየት ያካሄደችው ስኬታማ የምክክር ጉባዔ ልዩነቶችን በማጥበብ ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት ይጥላል ብለዋል።


 

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፈየራ ዲንሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ተጻራሪ ትርክቶችን በምክክር ወደ የጋራ አሸናፊነት ማምጣት የተቻለበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሀገራዊ ምክክር የተሻለ ዋጋ የሰጡ ሀገራት ወደ ተሻለ ሰላምና ዕድገት መምጣታቸውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያሳያሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን እንደ ምክክር ጉባዔው፣ ሕዳሴ ግድብና ዓድዋ ያሉ አኩሪ ድሎችን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኡባህ አደም (ዶ/ር)፣ የሀገራዊ የምክክር ጉባዔው በኢትዮጵያውያን መካከል መግባባት በመፍጠር ለሀገር ግንባታና ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ታሪካዊ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

በሂደቱ የተለያዩ ስሜቶችና የሀሳብ ልዩነቶች ቢንጸባረቁም፣ በመደማመጥና በመከባበር መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።

የብሔር፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶች የሕብረ ብሔራዊነት ጌጥ እንጂ የጥላቻ ምንጭ እንዳልሆኑ የገለጠ መድረክ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም