የአረጓዴ ዐሻራ እና የከተሞች ልማት በአካባቢ ጥበቃና የዜጎችን ጤና በመጠበቅ ለአፍሪካውያን በአርዓያነት የሚወሰዱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአረጓዴ ዐሻራ እና የከተሞች ልማት በአካባቢ ጥበቃና የዜጎችን ጤና በመጠበቅ ለአፍሪካውያን በአርዓያነት የሚወሰዱ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦የአረጓዴ ዐሻራ እና የከተሞች ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋምና የዜጎችን አካላዊና አዕምሯዊ ጤና በመጠበቅ ለአፍሪካውያን በአርዓያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቡባክሪ ዲያዎ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከ50 ቢሊዬን በላይ አይነተ ብዙ ችግኞችን መትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ያግዛል።
አዲስ አበባን ጨምሮ ከ70 በላይ በሚሆኑ ከተሞች በተዘረጋው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ፣ ጽዱና ተስማሚ እንዲሁም ለስራ ዕድል ፈጠራ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በብዘሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ ባከናወነቻቸው ሥራዎች ቱሪዝም ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ሆኖ ዕመርታ አስመዝግቧል።
መከላከልና አክሞ ማዳንን መሰረት አድርጎ በተሻሻለው የጤና ፖሊሲ በመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት የአፍሪካ ሞዴልነቷን በተግባር አሳይታለች።
በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቡባክሪ ዲያዎ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና አጠባበቅ ዕምርታዊ ለውጥ አስመዝግባለች።
ጤና ከማህበራዊ ወጭ ወደ ኢንቨስትመንት የሚቀየር ሀብት መሆኑን በመግለጽ፤ ዘላቂነት ያለው የጤና ሥርዓት ለመገንባት የጤና መሰረተ ልማት ግንባታን በፋይናንስ መደገፍ ይገባል ብለዋል።
ጤና ለአንድ ሀገር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት የላቀ መሆኑን በማንሳት፤ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት ያስመዘገበችው ስኬት ኢንቨስትመንት መሆኑ ገልጸዋል።
ጤና እና የአካባቢ ጥበቃ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን የገለጹት ሃላፊው፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በቢሊዬን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል አርዓያነት ያለው ሥራ አከናውናለች ብለዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለየዩ የሀገሪቱ ከተሞች የወንዝ ዳርቻዎችን በማልማት በአካልና በአዕምሮ ጤናማ ማህበረሰብ እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአረጓዴ ዐሻራ እና ከተሞች ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋምና ዜጎችን አካላዊና አዕምሯዊ ጤና የመጠበቅ ጥረቷን አፍሪካውያን በአርዓያነት ሊወስዱት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራና ከተሞች ልማት ሰዎች ንጹህ አየር እየተነፈሱ የሚንሸራሸሩበትን ከተማ እየገፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።
ይሄውም የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት በማሻሻል የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ ሳቢ የቱሪስት ማዕከል በማድረግ የኢኮኖሚ አቅሟን ያሳድጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች በእውነት ሊኮራባቸው የሚገቡ ናቸው ያሉት ሃላፊው፤ አፍሪካውያን ትምህርት በመውሰድ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑባት አህጉር መሆኗን ማሳየት ይገባናል ብለዋል።