የኢትዮጵያ ብዝኅ ሃይማኖታዊ እሴቶች የሕብረብሔራዊ አንድነት መገለጫና ሀገራዊ መግባባት ድልድዮች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብዝኅ ሃይማኖታዊ እሴቶች የሕብረብሔራዊ አንድነት መገለጫና ሀገራዊ መግባባት ድልድዮች ናቸው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብዝኅ ሃይማኖታዊ እሴቶች የሕብረብሔራዊ አንድነት መገለጫና ሀገራዊ መግባባት ድልድዮች መሆናቸውን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀች፣ ብዝኅ እምነቶች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር ናት።
የኢትዮጵያውያን ሕብረ ብሔራዊ ድምቀትም ሀገራቸውን በዓለም ላይ የአንድነትና መተሳሰብ የዘመናት ድምቀትና የወል ሃብት መገለጫ እንድትሆን ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በሃይማኖቶች መካከል ዘመናትን የተሻገረው ትስስርና ጥልቅ መስተጋብርም የሀገርን ሉዓላዊ ዳር ድንበር በማስጠበቅ መስዋዕትነት መክፈልን የሚጨምር የአብሮነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች የሰላም፣ አንድነትና ምክክር መንፈሳዊ አስተምህሮ መገለጫዎች ናቸው ያሉት ጸሐፊው፣ የእምነት አባቶችም ይህን እሴት በማስቀጠል የሀገራዊ መግባባት ድልድይ ሊገነቡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሁሉም ሃይማኖቶች የእርስ በርስ መስተጋብራቸውን በማጠናከር ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና አንድነት በማስጠበቅ፣ ሕብረ ብሔራዊነትን እንደ ጌጥና ልዩ ጸጋ የሚቆጥር ትውልድ ማፍራት የሚያስችል መሠረት እየተጣለ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን መዳከም የሚሹ የጥፋት ኃይሎችንም እኩይ ሴራቸውን በቅጡ በመገንዘብ፣ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላምና አንድነት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መድረኩም በቀጣዮቹ ጊዜያት በሰላም ግንባታ፣ በሕዝቦች አንድነት እንዲሁም በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋ የመቅረጽ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።