ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች ከአውሮፓ ህብረት የግሎባል ጌትዌይ ስትራቴጂ ትኩረት ጋር ይጣጣማል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች ከአውሮፓ ህብረት የግሎባል ጌትዌይ ስትራቴጂ ትኩረት ጋር ይጣጣማል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች ከአውሮፓ ህብረት የግሎባል ጌትዌይ ስትራቴጂ ትኩረት ከሆኑት የንጹህ ኢነርጂ፣ የዲጂታል ትስስር፣ የግብርና እሴት ሰንሰለት እና የመሠረተ ልማት ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚጣጣሙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር በመተባበር “ስልታዊ አጋርነት ለለውጥ፡ የአውሮፓ ህብረት ግሎባል ጌትዌይ እና የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ዘላቂ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት በመመራት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በኩል በርካታ መዋቅራዊ ለውጦች ተደርገዋል።
በዚህም የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ፣ የፊስካል ዲሲፕሊንን ማጠናከር እና ቀደም ሲል ለውጭ ውድድር ዝግ ሆነው የቆዩ ዘርፎችን ክፍት ማድረግን ጨምሮ መንግስት ከባድ ነገር ግን አስፈላጊ ውሳኔዎችን መውሰዱን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት የግሎባል ጌትዌይ ስትራቴጂ በንጹህ ኢነርጂ፣ በዲጂታል ትስስር፣ በግብርና እሴት ሰንሰለት እና በመሠረተ ልማት ላይ ትኩረት ማድረጉ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የልማት ቅድሚያዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚጣጣም አብራርተዋል።
ይህም በተቋማት አቅም ግንባታ እና ለሁለቱም ወገን በሚጠቅሙ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ራፊ አባራያ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ታሪካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት የግሎባል ጌትዌይ ማዕቀፍ በተለይም በዘላቂ መሠረተ ልማት፣ በንጹህ ኢነርጂ፣ በዲጂታል ትስስር፣ በግብርና-ምግብ እሴት ሰንሰለት እና በሰው ሀብት ልማት ላይ የሚሰጠው ትኩረት ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ጋር በእጅጉ እንደሚጣጣም አስረድተዋል።
ይህ የግሎባል ጌትዌይ ማዕቀፍ የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ማስገኘት ብቻ ሳይሆን፣ የተቋማትን አቅም ለማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማስፋፋት እና የሀገሪቷን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለመደገፍ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
መድረኩ ከሀሳብ ልውውጥ ባለፈ ሁለቱ ወገኖች የጋራ ጉዳዮች በመለየት ወደ ተጨባጭ የልማት ፕሮጀክቶች እና የኢንቨስትመንት ስራዎች የሚሸጋገሩበትን መንገድ የሚያመላክት ተግባራዊ ምክረ-ሐሳብ እንደሚያፈልቅ እምነታቸውን ገልጸዋል።