ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመመካከር ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመመካከር ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል
ሰመራ፣ነሀሴ 26/2018(ኢዜአ) :-ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመመካከር ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን በአፋር ክልል የዱብቲና የሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር መድረክ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በየደረጃው ማሳተፍ የቻለና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመምከር ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው።
ምክክሩ አሻጋሪ ጉዳዮች የተነሱበትና ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑም ተመላክቷል።
ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው በአፋር ክልል በአውሲ ረሱ ዞን የዱብቲ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ መድረኩ በሀገሪቱ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የፈነጠቀ ነው።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሉጌታ ወርቁ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በመመካከር ችግሮችን የመፍታት ባህልን ለማዳበር ጠንካራ መሰረት የጣሉበት ነው።
ይህ ሂደት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
ለልዩነቶች መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን ወደ መሐል አምጥቶ ለመፍታት መመካከር ብቸኛውና ወሳኙ መንገድ መሆኑን በተግባር ማረጋገጡንም አክለዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ መምህር ሸዋታጠቅ አደመ በበኩላቸው፤ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ተመካክረው ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችላቸውን አዲስ ምዕራፍ መክፈት የቻሉበት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮች እልባት እንዲያገኙ የሚያስችልና መጪው ጊዜ ለሀገሪቱ ብሩህ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።
የምክክር መድረኩ የቆዩ ባህላዊ የሰላም እሴቶችን እና የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን በዘመናዊ መንገድ ለመተግበርና ጥቅም ላይ ለማዋል ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል።
የሎጊያ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት የምክክር መድረኩ ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን የተሻለች ሀገር ለመገንባት ይበጃል ያሉትን ሀሳቦች ያዋጡበትና ሀገር ያሸነፈችበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምክክሩ ችግሮችን በስክነት የመፍታት ባህል እንዲጎለብትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው የሎጊያ ከተማ ነዋሪ አወል ኡመር ናቸው።
ምክክሩ የልዩነት ሀሳቦችን ለመፍታት የሐይል አማራጮች ስፍራ እንደሌላቸው ያረጋገጠ መሆኑን አስታውቀዋል።